የፕላንና ልማት ኮሚሽን እና የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን በዲጂታል ክትትልና ሪፖርት አቀራረብ ሥርዓት ዙሪያ የልምድ ልውውጥ አደረጉ

ነሃሴ1/2013(ዋልታ) – የኢፌዴሪ ፕላንና ልማት ኮሚሽን ከየአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ጋር በዲጂታል የክትትልና ሪፖርት አቀራርብ ሥርዓት (D~MRS) ዙሪያ የልምድ ልውውጥ አድርገዋል።

ይህ የልምድ ልውውጥ ጠቃሚ አሰራር ዘዴዎችን ከአንዱ ወደሌላው ለማስተላፍ እንዲሁም የሚኖሩ ጉድለቶችን እና ክፍተቶችን ለመሙላት የታሰበ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በዌብናር በመታገዝ በተካሄደው የልምድ ልውውጥ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የተዘጋጀው IPRT የተሰኘው ሥርዓት በዶ/ር ታደለ ፈረደ የቀረበ ሲሆን፣ በፕላንና ልማት ኮሚሽን የተዘጋጀው የዲጂታል ክትትልና ሪፖርት አቀራረብ ሥርዓት(D~MRS) በበፕላንና ልማት ኮሚሽን አማካሪ በሆኑት አቶ ሰለሞን ተስፋሥላሴ በኩል ቀርቧል።

በማስከተልም በሁለቱ የዲጂታል ክትትልና ሪፖርት አቀራርብ ሥርዓቶች ዙሪያ ውይይቶች ተደርጎ ከሁለቱም በኩል ማብራሪያዎች ተሰጥተዋል፡፡

የልምድ ልውውጡ ከአንደኛው ወገን ያለውን ክፍተት ከሌላው በመማር ክፍተቱን የማሟላት ዕድል እንዲፈጠር ከማድረጉም በላይ በክትትልና ግምገማ ሥርዓት ዙሪያ በተለይም የተቀናጀ  ዲጂታል የዕቅድ ክትትልና ግምገማ አሰራሮችን ለማጎልበት ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በመጨረሻም ሁለቱ ተቋማት ከዚሁ ጋር በተገናኘ በቀጣይ ትኩረት አድርገው በጋራ መስራት ያለባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡