ደራርቱ ቱሉ የስፖርት ማስልጠኛ እና ምርምር ኢንስቲትዩት ተመረቀ

ሐምሌ 11/2016 (አዲስ ዋልታ) በ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ወጪ የተገነባው ደራርቱ ቱሉ የስፖርት ማስልጠኛ እና ምርምር ኢንስቲትዩት በዛሬው ዕለት ተመረቀ።

የስፖርት ማስልጠኛ እና ምርምር ኢንስቲትዩቱ የ1992 ባርሴሎና እና የ2000 የሲድኒ ኢሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ ለሆነቸው ረዳት ኮሚሽነር አትሌት ደራርቱ ቱሉ መታሰቢያ ነው ተብሏል፡፡

በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሸገር ከተማ ሱልልታ ክፍለ ከተማ የተገነባው የስፖርት ማስልጠኛ እና ምርምር ኢንስቲትዩቱ ንቁና በስፖርት የዳበረ ትወልድ ለማፍራት ያግዛል ተብሏል።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ክልሉ በአትሌቲክሱ ለሀገራችን ትልቅ ሚናን እየተጫወተ መሆኑን ጠቅሰው ደራርቱ ከነዚህ አትሌቶች መካከል ቀዳማዋ ናት ብለዋል።
ኢንስቲትዩቱ ደግሞ የሷን ታሪክ እያዩ ለሚያድጉ ሀገርን ለሚያስጠሩ ስፖርተኞች መፍለቂያ ይሆናል ብለዋል።

ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ የስፖርት ማስልጠኛ እና የምርምር ኢንስቲትዩቱ ለኔ ከሰራሁት ታሪክ በላይ መሆኑን እና ለኢትዮጵያ ብሎም ለአፍሪካ የስፖርት እድገት ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብላለች።

የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ መንግስት ትልቅ በጀት በመመደብ እንደዚህ አይነት የስፖርት ማስልጠኛ መገንባቱ ለስፖርቱ ያለውን ቁርጠኝነ የሚያሳይ ነው ብለዋል ።

በጀግናዋ አትሌት ደራርቱ ቱሉ የተሰየመው ይህ የማስልጠኛ ኢንስቲትዩት በሀገራችን ግዙፍና በአይነቱ የተለየ ሲሆን የተለያዩ የስፖርት አይነት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን አካቶ ይዟል።

በምርቃ ስነ-ስረዓቱ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እና የስፖርት ቤተሰቡ ተገኝተዋል።

በለዊ በለጠ