በኢትዮጵያ የእንቁላልና የስጋ ዶሮ ምርት ቢኖርም ከፍተኛ ጥራት ያላቸው የዶሮ ዝርያዎችን በመጠቀም ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ እንደ ሀገር ያለው ተጠቃሚነት ዝቅተኛ ሆኖ ቆይቷል።
በ”የሌማት ትሩፋት” ኢኒሼቲቭ በሀገሪቱ የተጀመረው የዶሮ እርባታ ምርታማነትን ከፍ ለማድረግ የሚረዱ አዳዲስ ፕሮጀክቶች እንዲከፈቱ ምክንያት ሆኗል።
በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የእርሻ ዘርፍ የሆነው የኤልፎራ አግሮ-ኢንዱስትሪ ሻሎ የተቀናጀ እርሻ ልማት ዘመናዊ እና በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን የቅድመ ወላጅ (Grandparent Generation Chicken Farming) የዶሮ እርባታ ፕሮጀክት ማስጀመሩ የዚሁ አካል ነው።
የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዳውድ ኢብራሂም ለአዲስ ዋልታ ዲጂታል ሚዲያ እንደገለጹት ቅድመ ወላጅ ዶሮ ማለት አራት የዶሮ ዝርያዎች በአንድ ላይ አድገው ከሁለቱ ዝርያዎች የወንዱን ከሁለቱ ዝርያዎች ደግሞ የሴቷን በመውሰድ ወላጅ ዶሮ የሚፈጠርበት ሂደት ነው።
ወላጅ ዶሮ ሲባል ከአንድ ወንድ እና ከአንድ ሴት ዶሮ የሚወሰዱ በርካታ ጫጩቶችን በሀገር አቀፍ ደረጃ ማከፋፈል የሚቻልበት ሂደት ነው፡፡ ኢትዮጵያ እስካሁን እነዚህን ጫጩቶች ከፍተኛ ወጭ በማውጣት ከውጭ ስታስገባ ቆይታለች። በቀጣይ ግን ሀገሪቱ ከራሷ አልፋ ወደ ጎረቤት ሀገራት የመላክ እቅድም ይዛለች። የሌማት ቱርፋት በዶሮ ልማት ላይ ማነቆ የሆነበትም ችግር ይቀረፋል።
በቅድመ ወላጅ ዶሮ እጅግ በርካታ ወላጅ ዶሮዎችን ከማስገኘት በተጨማሪ በትንሽ ቁጥር ብዙ ጫጩቶችን ማግኘት የሚቻልበት ሁኔታ እንደሚፈጥር የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ገልጸዋል።
የቅድመ ወላጅ ዶሮ እርባታው የተሰራው በላቁ የዘረመል ባህሪያቸው የሚታወቁ ዶሮዎችን አባዝቶ ለገበያ ለማቅረብ ነው። ይህ የቅድመ ወላጅ ዶሮ እርባታ በንግድ ሰንሰለት ውስጥ የወላጅ ቀጥሎም የንግድ ዶሮዎችን በጥራት በማቅረብ ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡
የቅድመ ወላጅ ዶሮ እርባታ ከፍተኛ የእንቁላል እና የስጋ ምርት መስጠት የሚችሉ የዶሮ ዝርያዎችን በመጠቀም ጥራት ያለው የዶሮ ስጋ ምርት እና እንቁላል ጣይ ዶሮዎችን በከፍተኛ መጠን ማምረት የሚያስችል ነው።
በእድገት ጥራት፣ በሽታ በመከላከል እንዲሁም ከፍተኛ የስጋ እና የእንቁላል ምርት በመስጠት የሚታወቁ የተሻሻሉ የዶሮ ዝርያዎችን በመጠቀም በሚከናወነው በዚህ በዓይነቱ ዘመናዊ የሆነ የዶሮ እርባታ ዘዴ በርካታ ሀገራት ተጠቃሚ ሲሆኑ በኢትዮጵያም ተጀምሯል።
የቅድመ ወላጅ ዶሮ በየጊዜው ከውጭ ሲገባ በመቆየቱ ለግዥው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ያስፈልግ ነበር። ይህ ፕሮጀክትም የውጭ ምንዛሪን በማስቀረትና ዜጎች በተመጣጣኝ ዋጋ ጤንነታቸው የተጠበቀ የዶሮ ግብዓቶችን እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ ሚናው የጎላ ነው።
በብርሃኑ አበራ