ጤና ደጉ-በክረምት ሊከሰቱ የሚችሉ በሽታና አደጋዎች



በክረምት በአየር ጸባዩ ምክንያት የተለያዩ በሽታዎቸ እና አደጋዎች ይከሰታሉ። የዘንድሮው ክረምት በመግባት ላይ በመሆኑ በዚህ ወቅት ሊከሰቱ የሚችሉ በሽታዎችንና አደጋዎችን ለመጠቆም ወደድን።

ከሰኔ እስከ መስከረም አጋማሽ ባሉት ቀናት በብዛት የሚከሰቱት ዋና ዋና በሽታዎች እና አደጋዎችን እንመልከት።

ሀ. የወባ በሽታ

የወባ በሽታ በዋናነት በክረምት የሚከሰተው በሽታውን የምታስተላልፈው ሴቷ የወባ ትንኝ በብዛት የምትራባበት ወቅት በመሆኑ ነው። በዚህ ወቅት እንደ ረግረግ፣ ሞቃትና ወበቃማ የአየር ሁኔታ ትንኟ ለመራባት ስለሚያመቻት በሽታውን በብዛት እንዲሰራጭ ምክንያት ትሆናለች።

ለ. የጎርፍ አደጋ

በክረምት ወራት ከፍተኛ ዝናብ ስለሚዘንብ ጎርፍ መከሰቱ የሚጠበቅ ነው። ሆኖም ጎርፉ ሊፈስበት ከሚገባው ወንዝና ጅረት በመውጣት ሰው በሚኖርባቸው ቦታዎች ሲፈስ በንብረትና በሰው ህይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል። በአገራችን በተደጋጋሚ ጊዜ የጎርፍ አደጋዎች ተከስተው በርካታ የሰው ህይወት ማለፉና ንብረት መጎዳቱ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። በድሬዳዋ፣ በቅርቡ በሀላባ ዞን፣ በአፋር ክልልና በሌሎች የአገራችን ቦታዎች የጎርፍ አደጋ ተከስቶ ሰዎች ህይወታቸውን ማጣታቸው፣ መፈናቀላቸውና ንብረታቸው መውደሙ ይታወሳል።

ሐ. በከሰል ጭስ መመረዝ

ክረምት በተለይ በከፍተኛ ቦታዎች አየሩ ቀዝቃዛ በመሆኑ ሰዎች ቤታቸውን ለማሞቅ ከሰል ማቀጣጠል የተለመደ ተግባር ነው። ሙቀት ለመፍጠር በርና መስኮት በመዝጋት የከሰል ማቀጣጠሉ ተግበር ካርቦን ሞኖኦክሳይድ የተባለ መርዛማ ጭስ እንዲፈጠር ያደርጋል። ጭሱ መርዛማ በመሆኑ ሰዎች በደማቸው ውስጥ የኦክስጅን እጥረት እንዲፈጠር በማድረግ ለከፍተኛ ጉዳትና ሞት ይዳርጋል።

መ. የምግብ መመረዝ

ክረምት በጎርፍ ምክንያት ውሃ እንዲበከል ሰፊ ዕድል ይፈጥራል። ድፍርስ ውሃ በተሰበሩና ባረጁ ቧንቧዎች በመስረግ የመጠጥ ውሃችንን ሊበክል ይችላል። ይህም ለታይፎይድና ሌሎች ምግብና መጠጥ ወለድ በሽታዎች መንስኤ ሊሆን ይችላል።



ሠ. የመተንፈሻ አካላት ህመም

ክረምት በተለይ በዝቅተኛና ሞቃታማ ቦታዎች ወበቃማ የአየር ሁኔታ ስለሚፈጥር ይህም በመተንፈሻ አካላቶቻችን ላይ በሽታ አምጭ ተህዋሲያን ለማደግ ምቹ ሁኔታን ይፈጥርላቸዋል። ሳይነስና የቅዝቃዜ አለርጂ እንዲሁም አስም ያለባቸው ሰዎችም በክረምት ወራት የጤና እክል ይገጥማቸዋል።

ረ. የመኪና አደጋ

በክረምት ወቅት በሚኖር ዝናብና ጭጋግ ምክንያት የመኪና አደጋዎች ይበዛሉ። አደጋዎቹ የሚፈጠሩት አንድም በአየር ሁኔታው (እርጥበት፣ አዳላጭ/አንሸራታችና ለዕይታ የሚያስቸግር የአየር ሁኔታ መኖር) በሌላም በኩል ከመኪኖች የቴክኒክ ብቃት ችግር (የዝናብ መጥረጊያ አለመስራት/አለመኖር፣ ጥርሱ ያለቀ ጎማ መጠቀም፣ ወደ ኋላ መመለከቻ መስታወት በዝናብ መሸፈን ወዘተ) ምክንያት ነው።

ሠ. ሌሎች አደጋዎች

በዝናባማዎቹ የክረምት ወራት እንደ መሬት መንሸራተት፣ የኤሌክትሪክና የመብረቅ አደጋዎችም በብዛት የሚፈጠሩበት ወቅት ነው። በከፍተኛ ዝናብና ነፋስ ምክንያት የኤሌክትሪክ መስመሮች የመበጠስና ርጥብ መሬት ላይ ሲያርፉ በሰዎች ላይ እስከሞት የሚደርስ ጉዳት ያስከትላል።

ከላይ የተዘረዘሩትም ሆነ ሌሎች ያልተጠቀሱ ከከረምት ወቅት ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ በሽታዎችና አደጋዎችን ለመከላከል አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው እንላለን።

በቴዎድሮስ ሳህለ