ጤና ደጉ – በየቀኑ በቂ ውሃ የመጠጣት ጠቀሜታዎች

ውሃ ህይወት ላላቸው ነገሮች ሁሉ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። ከስልሳ በመቶ (60%) በላይ ሰውነታችን በፈሳሽ የተሞላ ሲሆን የደማችን 90 በመቶ የሚሆነው ደግሞ ውሃ ነው። በመሆኑም በየቀኑ በበቂ ውሃ በመጠጣት የፈሳሽ መጠናችንን መጠበቅ ይገባል።

በቀን ልንጠጣው የሚገባን የውሃ መጠን ላይ ግልፅ የሆነ መጠን ለማስቀመጥ አስቸጋሪ ቢሆንም አንዳንድ ጥናቶች በቀን እስከ 8 ብርጭቆ ውሃ መጠጣት እንዳለብን ይመክራሉ።

የውሃው መጠን ከሰው ሰው፣ ከምንኖርበት አየር ንብረት፣ ከስራችን ባህርይ፣ ከጤናችን ሁኔታና እድሜን መሰረት በማድረግ የተለያየ ቢሆንም በቀን በበቂ መጠን ውሃ የመጠጣት አስፈላጊነት ግን አያከራክርም።

በመሆኑም በሞቃት አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች፣ እንቅስቃሴና የጉልበት ስራዎች የሚሰሩ ሰዎች፣ ትኩሳት ያለባቸው እና ተቅማጥና ትውከት የገጠማቸው ሰዎች ብዙ ውሃ መጠጣት ይጠበቅባቸዋል።

ለመሆኑ በቀን በቂ መጠን ውሃ መጠጣት ለሰውነታችን ምን ምን ጠቀሜታ አለው?

• ኦክስጅንና የምግብ ንጥረ ነገሮች ወደ ህዋሶቻችን ያጓጉዛል
• የምግብ ልመትን ያግዛል
• የደም ግፊትን ያረጋጋል
• መገጣጠሚያ አንዳይጎዳ ያለሰልሳል
• የውስጥ አካልን ለመንከባከብ ይረዳል
• የሰውነትን የሙቀት መጠን ሚዛን ይጠብቃል
• የሆድ ድርቀትን ይከላከላል
• የቆዳን ጤንነት ለመጠበቅ ይጠቅማል
• ከሰውነታችን ጎጅና ጥቅም የሌላቸውን ነገሮች በላብና በሽንት መልክ ያስወግዳል
• ባክቴሪያዎችን ከሽንት ፊኛችን አጥቦ ለማስወጣት እንደሚጠቅም ሃርቫርድ ሄልዝ ያወጣው መረጃ ጠቁማል።

ስለውሃ ተጨማሪ ምከረ ሃሳቦች

• የምንጠጣው ፈሳሽ ስኳርና ጣዕም ከሚኖረው ይልቅ ንጹህ ውሃ ቢሆን ይመረጣል
• ከሞቀ ይልቅ ቀዝቀዝ ያለ ውሃ መጠጣት ይመከራል
• ምግብ በምንመገብበት ወቅት ሁሉ ውሃ አብሮ ማቅረብ ተገቢ ነው
• አካባቢ የሚበክሉ የውሃ መያዣዎችን ከመጠቀም መልሰን ልንጠቀምባቸው የምንችላቸውን ጠርሙሶች ምርጫችን ብናደርግ በብዙ መልኩ ጠቀሜታው የጎላ ነው።