ጤና ደጉ – የወባ በሽታ



ወባ ፕላዝሞዲዬም በተባለ ጥገኛ ተሕዋስያን ምክንያት የሚመጣ አደገኛ በሽታ ነው። በሽታው በዚህ ተሕዋሲያን በተጠቃች የወባ ትንኝ አማካኝነት ወደ ሰው ይተላለፋል። ተሕዋስያኑ ወደ ሰው ጉበት ህዋሶች ውስጥ በመግባትና በመራባታ እንድንታመም ያደርጋሉ።

ፋልሲፓረም፣ ቫይቫክስ፣ ኦቫሌ እና ማላሪዬ የተባሉ አራት ዓይነት የወባ በሽታ ዝርያ አሉ። የበሽታው ተሕዋሲያን አኖፌለስ በተባለችው ሴቷ የወባ ትንኝ አማካኝነት ወደ ሰው ታስተላልፋለች። እንደ ማላሪያ ጆርናል መረጃ በአገራችን 72 ከመቶ የወባ በሽታ ዓይነት ፋልሲፓረም ሲሆን ቫይቫክስ ደግሞ 23 በመቶ የሚሆነውን ይሸፍናል።

በፈረንጆቹ 2022 ብቻ 249 ሚሊዮን ሰዎች በበሽታው መያዛቸው የተመዘገበ ሲሆን 608 ሺሕ ለሚሆኑ ሰዎች ሞት ምክንያት መሆኑን መረጃው ያመለክታል።

ከ5 ዓመት በታች ዕድሜ ያላቸው ህጻናት፣ ነፍሰጡር ሴቶች እና ኤችአይቪ በደማቸው ውስጥ ያለ ሰዎች ለወባ በሽታ ያላቸው ተጋላጭነት ከፍ ያለ ነው። በእርግዝና ወቅት በወባ የተጠቁ እናቶች ያለ ጊዜ ለሚከሰት ምጥ እና ወሊድ እንዲሁም ልጅ ሲወለድ ከመጠን ያነሰ ክብደት እንዲኖረው ይዳረጋሉ።

በሽታው በትሮፒካል አካባቢ የዓለም ክፍል የሚከሰት ሲሆን በተለይ አፍሪካ ወባ በስፋት ከሚከሰትባቸው የዓለም ክፍል ግንባር ቀደም ነው። የወባ በሽታ 94 በመቶው የሚከሰተው እና ከሟቾቹም 95 በመቶው የሚሆነው ህዝብ ከዚሁ አህጉር መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል።

በአፍሪካ ናይጀሪያ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ፣ ዩጋንዳና ሞዛምቢክ በወባ በሽታ ከሚሞቱት ሰዎች ግማሹን እንደሚሸፍኑ መረጃው ጨምሮ ጠቅሷል።

የወባ በሽታ እና ድህነት እጅግ የተሳሰሩ ናቸው። ወባ በድህነት እና በጤና እክል ውስጥ ላሉ በጣም ድሃ ሀገራት እና ማህበረሰቦች በቀላሉ መስፋፋትና ጉዳት ማድረስ ይችላል። በድህነት በሚማቅቅ ማህበረሰብ ዘንድ በሽታውን ቀድሞ ለመከላከልም ሆነ አፋጣኝ ህክምና ለማግኘት እጅ አጠር በመሆናቸው ተጋላጭነታቸውን ከፍ ያደርገዋል።

እንደ ድርጅቱ መረጃ ኢትዮጵያ በሽታው በብዛት ከሚከሰትባቸው 15 አገራት ዝርዝር ውስጥ ስትሆን በፈረንጆቹ 2020 ብቻ በዓለም ላይ ከተከሰተው የወባ ህመምና ሞት 1 ነጥብ 7 ያህሉ በአገራችን የተያዘ እንደነበር ነው ያመለከተው።

የወባ በሽታ በኢትዮጵያ ከነሐሴ እስከ ህዳር መጨረሻ ባሉት ወራት በስፋት የሚከሰትበት ወቅት ሲሆን በአንዳንድ ቦታዎች በሚያዚያና ግንቦት ጭምር በተወሰነ መጠን ይከሰታል።

የወባ በሽታን እንዳይከሰት መከላከልና ከተከሰተም አክሞ ማዳን ይቻልላ። በአሁኑ ወቅት ለበሽታው ክትባት እየተዘጋጀ ሲሆን በቅርቡ አገልግሎት ላይ ይውላል ተብሎ ይጠበቃል።

የበሽታው ምልክቶች፡-

ከፍተኛ ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለትና ማንቀጥቀጥ፣ ማላብ፣ ቁርጥማት፣ ራስ ምታት፣ ማቅለሽለሽና ማስመለስ የወባ በሽታ ምልክቶች ናቸው። ከፍተኛ ድካም፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ ውሃ ጥም ወዘተ… ተጨማሪ ምልክቶች።

በጊዜ ህክምና ካላደረግን በደማችን ውስጥ ያለው የወባ ጥገኛ ተሕዋሲያን በዝቶና ጎልብቶ ሳንባችን፣ ጉበታችን፣ ኩላሊታችን እና አንጎላችን ላይ ጉዳት ከማድረሱ ባሻገር የኩላሊት ጉዳት፣ ኮማ፣ ራስን መሳት፣ የሽንት መጥቆር፣ የመተንፈስ ችግር ወዘተ… ሊያስከትል ይችላል።

ምልክቶቹ ከ48 እስከ 72 ሰዓት እየቆዩ በድጋሚ ይታያሉ። ይህን የሚወስነው ግለሰቡን ያጠቁት ተሕዋስያን ዓይነትና በበሽታው ተይዞ የቆየበት ጊዜ ነው።

የወባ በሽታ መከላከያ መንገዶች፡-

• በጸረ ትንኝ የተነከረ አጎበር መጠቀም
• ቆሻሻን በትክክል ማስወገድ
• ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን ማድረቅና የወባ ትንኝ መራቢያ ቦታን ማሳጣት

ምንጭ፡-

• የዓለም ጤና ድርጅት
• ኢን አይ ኤች
• ማላሪያ ጆርናል
• ሃኪም