13ኛዋ ‹‹የምህረት ወር›› ጳጉሜ

13ኛዋ ‹‹የምህረት ወር›› ጳጉሜ

(በአመለወርቅ መኳንንት)

ኢትዮጵያ ከሌላው ዓለም በተለየ የራሷ የዘመን ሥሌትና ቀመር ያላት ጥንታዊት አገር ናት።

የክረምቱ ወቅት የሚፈጥረው ዝናባማ፣ ብርዳማ አየር ሁኔታ ተገልጦ ተስፋ ከብርሃናማ የሰማይ ድምቀት እና ከምድሯ ልምላሜ እና የአደይ አበባ ፍካት ጋር ተደማምሮ በሕዝቧ የአኗኗር ባህል ውስጥ የኖረ፣ ያለና የዳበር ልዩ የአዲስ ዓመት ክብረ በዓልም አላት።

ባህላዊ ጨዋታዎች፣ ተስፋ የሚፈነጠቅባት የጳጉሜ መጨረሻ እና የመስከረም መጀመሪያን ታክኮ የሚገለጠው የአገሬው ሕይወት በግላጭ ይታያል፣ ይደመጣል ፣ ይሸተታል፣ ይቀመሳልም።

ኢትዮጵያዊያን የአዲስ ዓመት ጅማሮ ወቅታቸውን ሕፃን አዛውንት፣ ሴት ወንድ ሳይሉ በደስታ፣ በፍቅር ተሰባስበው «እንኳን አደረሰህ አደረሰሽ፣ መልካም አዲስ ዓመት፣ የሰላምና የጤና ዘመን ይሁንልን» እየተባባሉ ያልኖሩትን ነገን በጎ ሆኖ እንዲጠብቃቸው እርስ በእርስ መልካም ምኞታቸውንም ይገላለፃሉ።

ኢትዮጵያ በዓለም ብቸኛዋ የ13 ወራት ጸጋ ባለቤት ስትሆን የጳጉሜ ወርም በኢትዮጵያዊያን ዘንድ የምህረት ወር ተብሎ ይታመናል።

በተለይም  በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምሮ መሰረት ፀሎት የሚያርግበት እለተ ምፅዓት የሚታሰብበት የምህረት ወር ነው ይላሉ ከዋልታ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሃይማኖቱ መምህር መጋቤ ሀዲስ ሮዳስ ታደሰ (ዶ/ር)፡፡

ጳጉሜ በነሐሴ እና በመስከረም መካከል የሚገኝ ከአስራ ሦስቱ የኢትዮጵያ የወራት አቆጣጠር ውስጥ የመጨረሻው እና አሥራ ሦስተኛው  ነው።

ጳጉሜ በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠርም ዘመነ ዮሐንስ፣ ዘመነ ልቋስ  ዘመነ ማቴዎስ እና ዘመነ ማርቆስ በመባል ልዩ ሀይማኖታዊ ትርጓሜዎች አሉት ሲሉ መጋቤ ሀዲስ ሮዳስ ታደሰ (ዶ/ር) ይገልጻሉ፡፡

በተለይም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት መሰረት ምዕመናኑ በጳጉሜ ፀበል በመጠመቅ የሚያሳልፍበት የምህረት ወር መሆኑንም መጋቤ ሀዲስ ያብራራሉ፡፡

በተለይም ጳጉሜ 5 እና ልደተ ክርስቶስ የሚመጋገቡ እና የሚነፃፀሩ ናቸው ይላሉ መጋቤ ሀዲስ፡፡ አክለውም አዲስ ዓመት ተስፋ የሚሰነቅበት የጳጉሜን መጨረሻ እና የመስከረም መጀመሪያን አስታኮ የሚገለጠውን ወቅት ሰርግ በጭብጨባው መስከረም በአበባው ሲሉ ያስተሳስሩታል፡፡

የጳጉሜን አመጣጥ ስናይ በቀደምት ኢትዮጵያዊያን ሊቃውንት ጥልቅ ጥናት 1 እለት 24 ሰዓት ከ52 ካልኢት ከ31 ሳልሲት ነው ከሚለው እሳቤ የሚመዘዝ ሆኖ እናገኘዋለን።

ይህን ለማወቅ የዘርፉ ምሁራን 52 ካልኢት ስንት ነው? በዚህ ስሌት 1 ካልኢት = 24 ሴኮንድ ነው። ስለዚህ 52ቱ ካልኢቶች 1248 ሴኮንድ ይሆናሉ። (24X52=1248) = 20 ደቂቃ ከ48 ሴኮንድ 31 ሳልሲት ደግሞ 1 ሴኮንድ 2.5 ሳልሲት ስለሆነ =31/2.5 =12.4 ሴኮንድ ባጠቃላይ 20 ደቂቃ + 48 ሴኮንድ + 12.4 ሴኮንድ =20 ደቂቃ + 60.4 ሴኮንድ =21 ደቂቃ ከ0.4 ሴኮንድ የሚል ረቂቅ ስሌትን ያመጣሉ፡፡ ስለዚህም ይህንን ትርፍ አደማምረው 5 ቀናት ያሏትን የጳጉሜ ወር ይፈጥራሉ፡፡ በእርግጥ ጳጉሜ በ4 ዓመት አንድ ጊዜ 6፤ በ600 ዓመት አንድ ጊዜ ደግሞ 7 ቀን የምትሆን አስገራሚ ወርም ናት፡፡