ፊፋ በዘረኝነት ተግባር በሚሳተፉ ላይ ጠንከር ያለ ቅጣት ሊጥል ነው

በእግር ኳስ እየተባባሰ የመጣውን የዘረኝነት ተግባር ለማስወገድ በአባል ፌደሬሽኖች ከሚጣሉ ቅጣቶች በተጨማሪ የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር ጠንከር ያለ ቅጣት እንደሚያሳልፍ አስታውቋል፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን ለዩሮ 2020 ዋንጫ ማጣሪያ ከቡልጋሪያ አቻው በነበረው ጨዋታ የእንግሊዝ ተጫዋቾች ላይ አንዳንድ የቡልጋሪያ ደጋፊዎች የዘረኝነት ጥቃት በማድረሳቸው የዕለቱ ጨዋታ ሁለት ጊዜ መቋረጡ ይታወሳል፡፡

ድርጊቱ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ከማስቆጣቱም በላይ እግር ኳስ አሁንም የዘረኝነት ጥቃት ሰለባ ሆኖ መቀጠሉን ያሳየ ተግባር ሆኖ አልፏል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር የቡልጋሪያ ደጋፊዎች በእንግሊዝ ጥቁር ተጫዋቾች ላይ የዘረኝት ጥቃት በማድረሳቸው ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ምርመራ መጀመሩን አስታውቋል፡፡

የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማህበር ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ይህ አይነቱን ስፖርታዊ ጨዋነት የጎደላቸው ተግባር በሚፈፅሙ ላይ ተጨማሪ ዓለም አቀፍ እገዳ እንደሚያሳልፉ ገልፀዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ፊፋ ለዘረኝነት ምንም ቦታ እንደሌለው ጠቁመው የተቋሙ አባል ፌሬሽኖችና አመራሮች የዘረኝነት ጥቃትን ለመከላከል የተለያዩ ስልቶችን ቀይሰው እንዲንቀሳቀሱ ጠይቀዋል፡፡

ምንጭ፡ – ፊፋ