2ኛው የኦሮሚያ ክልል የታዳጊዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተጀመረ

ሁለተኛው የኦሮሚያ ክልል የታዳጊዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ በአሰላ ከተማ ተጀምሯል፡፡

የኦሮሚያ ክልል የታዳጊዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ በአሰላ ስታዲየም የተጀመረ ሲሆን እስከ የካቲት ሰባት ድረስ በተለያዩ ውድድሮች ይቀጥላል፡፡

በሻምፒዮናው በክልሉ የሚገኙ የታዳጊ ስልጠና ማዕከላት፣ ኘሮጀክቶች፣ ዞኖች እና ከተማ አስተዳደሮችን ጨምሮ ሌሎችም ይሳተፋሉ፡፡

በተለያዩ የውድድር ዓይነቶች በሁለቱም ፆታዎች ከ700 በላይ አትሌቶች የሚፎካከሩበት ሻምፒዮናው የታዳጊ ኘሮጀክቶችን ወቅታዊ አቋም የመመዘን አላማ አለው፡፡

በተጨማሪም በውድድሩ ውጤታማ የሚሆኑ አትሌቶች ክልሉን ወክለው በኢትዮጵያ ሻምፒዮና የሚሳተፉ ሲሆን ክለቦችም ስፖርተኞችን ለመምረጥ ይጠቀሙበታል፡፡

በሻምፒዮናው ዛሬ የፍጻሜና የማጣሪያ ውድድሮች ሲከናወኑ፣ የአሎሎ ውርወራና የርዝመት ዝላይን ጨምሮ የተለያዩ የመምና የሜዳ ላይ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል የታዳጊዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሁለት የእድሜ ምድቦች የሚከናወን ሲሆን ከ18 እና ከ16 ዓመት በታች በሚል የተከፈለ ነው፡፡

(በፍስሐ ጌትነት)