2 ሺሕ 800 የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች

ጳጉሜ 1/2013 (ዋልታ) በ2013 በጀት ዓመት በኢትዮጵያ የሳይበር ምኅዳር ላይ የተሰነዘሩ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች መጠን በእጥፍ መጨመሩን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ አስታወቀ።
በኤጀንሲው ብሔራዊ የሳይበር ጥቃት የአደጋ ዝግጁነት እና ምላሽ መስጫ ዲቪዥን ኃላፊ ሰብለወይን ጸጋዬ በ2013 በጀት ዓመት ከ2 ሺሕ 800 በላይ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ተሰንዝረዋል ብለዋል።
ይህም በ2012 ከተሞከረው 1 ሺሕ 80 ጥቃቶች ጋር ሲነፃፀር በእጥፍ መጨመሩን ያመላክታል ነው ያሉት።
ተቋማት አሰራራቸውን ቀደም ሲል ከነበረው ተለምዷዊ አጠቃቀም የበይነ መረብ አማራጮችን በስፋት መጠቀም መጀመራቸው፣ ከኅዳሴ ግድብ 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌት ጋር በተያያዘ በሳይበር አማካኝነት ጫናዎች መፈጠራቸው እና በበርካታ ተቋማት ዘንድ ያለው የሳይበር ደኅንነት ንቃተ ህሊና ክፍተት ለጥቃቶቹ መጨመር ምክንያት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ከሳይበር ጥቃት ሙከራዎች ውስጥ 75 ነጥብ 25 በመቶ ምላሽ የተሰጠባቸው ሲሆኑ፤ ቀሪዎቹ ደግሞ ምላሽ እየተሰጣባቸው ያሉ መሆናቸውን ከኤጀንሲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡