ተቋሙ በሩብ ዓመቱ ከ374 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር መሥጠቱን አስታወቀ

የአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም ባለፉት ሦስት ወራት ከ374 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር  ማከፈፈሉን  አስታወቀ ።  

የአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወይዘሮ ምዕራፍ አለማየሁ ለዋልታ እንደገለጹት ተቋሙ ባለፉት ሦስት ወራት 9ሺ454 ለሚሆኑ ተበዳሪዎች 435 ሚሊዮን 925 ሺ 27 ብር ብድር ለመሥጠት አቅዶ  ለ5,888 ተበዳሪዎች ብር 374 ሚሊዮን 857ሺ 700 ብር ብድር ማከፋፈል ተችሏል። 

በሩብ ዓመቱ ከተቋሙ ብድር የወሰዱት በማኑፋክቸሪንግ ፣በኮንስትራክሽን ፣ በአገልግሎት፣ በንግድ፣ በከተማ ግብርና በትራንስፖርት ዘርፎች የተሠማሩ ነዋሪዎች መሆናቸውን የጠቆሙት ወይዘሮ ምዕራፍ በአገልግሎትና በንግድ ዘርፍ የተሠማሩት ዜጎች ከፍተኛውን ብድር መጠን ማግኘት ችለዋል ብለዋል ።

ወጣቶችና ሴቶች ተቋሙ ከሚሠጠው ብድር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የሚገልጹት  ወይዘሮ ምዕራፍ  በሩብ  ዓመቱ ሴቶች 46.6 በመቶ ወጣቶች 37 ነጥብ 7 በመቶ  የብድር አገልግሎቱ ተጠቃሚ ሆነዋል ።  

ተቋሙ በሩብ ዓመቱ ብቻ 306 ሚሊዮን 33ሺ 26 ብር በቁጠባ መልክ ለመሰብሰብ አቅዶ በአጠቃላይ 324 ሚሊዮን 647ሺ687 ብር ወይም የዕቅዱን 106 በመቶ ለመሰብሰብ መቻሉንም ወይዘሮ ምዕራፍ አያይዘው ገልጸዋል ።

አዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም በ1993 ዓም የተቋቋመ ሲሆን ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል እያንቀሳቀሰ  ይገኛል ።