የአሜሪካ የንግድ ምክር ቤት በአዲስ አበባ ተከፈተ

የአሜሪካ የንግድ ምክር ቤት በአዲስ አበባ ተከፍቷል።

የአሜሪካ የንግድ ምክር ቤት በኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት አቶ ዳንኤል ኃይሉ እንዳሉት፤ ምክር ቤቱ የአሜሪካና የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንትና የንግድ ግንኙነት ለማጠናከር ያስችላል።

በኢትዮጵያና በአፍሪካ አገራት በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች በተሰማሩ የአሜሪካ ኩባንያዎች ትብብር የተቋቋመው ምክር ቤቱ የኩባንያዎቹ ባለቤቶች በንግድ ዘርፍ ያላቸውን ልምድ በመጠቀም የሎጅስቲክ ወጪ ለመቀነስና ለሥራ የሚያስፈልገውን የሠው ኃይል ለመመጠን የሚያስችል ምክክር እንዲያደርጉ እንደሚያግዝ አመልክቷል ።

የፋይናንስ ፍሰቱን በመረዳትና ከውጭ ምንዛሪ ጋር የተያያዙ ችግሮችን በመለየት ከመንግሥት ጋር በጋራ በመሆን ለችግሮቹ መፍትሄ ለማምጣት እንደሚሠራም ነው የተጠቆሙት።

ምክር ቤቱ በአሜሪካና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን የኢንቨስትመንትና የንግድ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ይሰራል ።

በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ሥራዎች በምን መልኩ እንደሚተገበሩ ምክር ቤቱ ለአዳዲስ ኩባንያዎች ያስተዋውቃል ነው ያሉት ።

ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ሥራ ላይ ልምድ ያላቸው ኩባንያዎች ልምዳቸውን አዲስ ለሚመጡ ኩባንያዎች የሚያስተላልፉበት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠርም ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።