ልማት ባንክ አቋርጦ የነበረውን የእርሻ ብድር አገልግሎት ጀመረ

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አቋርጦ የነበረውን የእርሻ ፕሮጀክት ብድር አገልግሎት  መጀመሩን  አስታወቀ ።

በኢትዮጵያ ልማት ባንክ የኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ  ምስጋናው  እንደገለጹት ባንኩ ከባለፈው የበጀት ዓመት መጋቢት ወር ጀምሮ እንዲቆም ያደረገውን በዝናብ የሚለሙ የእርሻ ብድሮችን ፋይናንስ ማድረግ ከጥር 25 / 2009 ዓም ጀምሮ እንዲቀጥል ወስኗል ።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በሰፋፊ እርሻዎች ለተሠማሩ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ ሲያደርግ የቆየ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ኃይሉ ዓምና የተለያዩ ሰብሎችን በዝናብ ለሚያለሙ ፕሮጀክቶች የሚሠጠው የብድርና ቴክኒክ ድጋፍ እንዲቆም መደረጉን አስታውሰዋል ።

ባንኩና የሚመለከታቸው የባለድርሻ አካላት በዝናብ የሚለሙ የእርሻ ፕሮጀክቶች ለተለያዩ የውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች የተጋለጡ በመሆናቸው ምክንያት የሚደርሰውን ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ለመቀነስ ለጊዜው ቢሆንም የሚሠጠውን ብድር ድጋፍ ማቋረጡን አስረድተዋል ።

መንግሥት፣ ባንኩና የባለድርሻ አካላት በጋራ በመሆን ሁኔታውን ሲገመግሙ ቆይተው ለተፈጠሩት ችግሮች  መፍትሄ የሚሆን የአሠራር ሥርዓትን በመዘርጋት በዝናብ የሚለሙ  የእርሻ ፕሮጀክቶችን የብድር ድጋፍ አገልግሎቱ እንዲጀመር  ውሳኔ ላይ ተደርሷል ። 

 የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የብድር ድጋፍ  ከሚያደርግላቸው  የእርሻ  ፕሮጀክቶች መካከል የተለያዩ ሰብሎችን  በዝናብ ውሃ የሚያለሙት የእርሻ ፕሮጀክቶች ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዙ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል  ዘግቧል ።