የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በግማሽ ዓመቱ የሥራ አፈጻጸም 71 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ ።
በባለሥልጣኑ የትምህርትና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም መኮንን ለዋልታ እንደገለጹት ባለሥልጣኑ ባለፉት ስድስት ወራት በአጠቃላይ 82 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ 71 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ ተችሏል ።
ባለሥልጣኑ በግማሽ ዓመቱ ገቢውን የሰበሰበው ከአገር ውስጥ ግብር ፣ ከወጪ ንግድ ቀረጥና ግብር እንዲሁም ከብሔራዊ ሎተሪ መሆኑን አቶ አፍሬም ተናግረዋል ።
በአጠቃላይ ከግብርና ከቀረጥ የተገኘው ገቢ ከዓምና ጋር ሲነጻጻር የ11 በመቶ እንዳለውም አቶ ኤፍሬም አያይዘው ገልጸዋል ።
ባለሥልጣኑ የኮንትሮባንድ ንግድን ለመቆጣጣር በግማሽ ዓመቱ በወሰዳቸው እርምጃዎች በአጠቃላይ በህገ ወጥ መልኩ ወደ አገር ውስጥ ሲገቡና ሲወጡ የተያዙ 428 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የተለያዩ እቃዎች እንዲወረሱ ተደርጓል ።
የግብር ከፋዩ ህብረተሰብ ግብርን መክፈል ግዴታው መሆኑን ተረድቶ የሚጠበቅበትን ክፍያ እንዲፈጽም ለማድረግ በግማሽ ዓመቱ የውይይት መድረክና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን አመልክተዋል ።
የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የጣት አሻራ ከግብር ከፋዩ በመውሰድ፣ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያዎችን በማስፋፋትና የጉምሩክ አገልግሎት መስጪያ መሣሪያዎችን የማዘመን ሥራዎች መካሄዳቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ።