ኢትዮ-ቴሌኮም በዘንድሮ የበጀት ዓመት የግማሽ ዓመት ከተለያዩ አገልግሎቶች በአጠቃላይ 15 ነጥብ 64 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ ።
የኢትዮ ቴሌኮም የኮርፖሬት ኮሚኒኬሽን ኦፊሰር አቶ አብዱራሂም አህመድ ለዋልታ እንደገለጹት የኩባንያው ገቢ ካለፈው የበጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር የ17በመቶ ዕድገት ተመዝግቧል ።
ኢትዮ-ቴሌኮም በግማሽ ዓመቱ ያልተጣራ ትርፍ መጠን በአጠቃላይ 11 ነጥብ 91 ቢሊዮን መሆኑን የጠቆሙት አቶ አብዱራሂም የተገኘው የተጣራ ትርፍ ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር የ18 በመቶ ዕድገት አሳይቷል ብለዋል ።
በአጠቃላይ በግማሽ ዓመቱ ከተለያዩ አገልግሎቶች ከተገኘው ገቢ ውስጥ 74 ነጥብ 5 በመቶ የሚሆነው ከሞባይል አገልገሎት፣ 14 በመቶው ከዳታና ኢንተርኔት እንዲሁም 7 በመቶ ገቢ ከዓለም አቀፍ አገልግሎቶች የተገኘ መሆኑን አቶ አብዱራሂም አስረድተዋል ።
እንደ አቶ አብዲራሂም ገለጻ በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ የኢትዮ – ቴሌኮም ደንበኞች ብዛት ከ 52 ሚሊዮን በላይ የደረሰ መሆኑንና ከዚህም ውስጥ 51 ሚሊዮን የሚሆኑት የሞባይል አገልግሎት ተጠቃሚዎች ሲሆኑ 14 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚሆኑት የኢንተርኔትና ዳታ አገልግሎት ተጠቃሚ ናቸው ።
ኢትዮ- ቴሌኮም የአገሪቱን የቴሌኮም መሠረተ ልማት ደህንነትን ከማረጋገጥና የቴሌኮም ማጭበርበርን ከመከላከል አንጻር የህብረተሰቡን ግንዛቤ ከማሳደግ ጎን ለጎን በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ፡፡