አዲስ አበባ ከተማ በየጊዜው በነዳጅ ማደያዎች የሚያጋጥመውን የተሸከርካሪዎች ሰልፍ ለማቃለል 60 አዳዲስ ነዳጅ ማደያዎች ግንባታ ለማከናወን የሚያስችል ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡
የማዕድን፣ የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ሞቱማ መቃሳ እንዳስታወቁት፤ በከተማዋ ብቻ ሳይሆን እንደ አገር ያሉት ነዳጅ ማደያዎች ቁጥር በጣም አነስተኛ ነው፡፡
ለዚህም በቂ የሆነ የመሬት አቅርቦት አለመኖር እንደ አንድ ምክንያት ጠቅሰዋል፡፡
ይሄን የነዳጅ ማደያዎች እጥረት በመገንዘብ ስልሳ አዳዲስ ማደያዎችን ለመገንባት የሚያስችል ቦታ ለማዘጋጀት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር መስማማታቸውን ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ አረጋግጠዋል፡፡
ማደያዎችን ከአዲስ አበባ ከተማ በተጨማሪ ችግሩ በሚስተዋልባቸው ሌሎች ከተሞችም መገንባት አስፈላጊ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ ዘርፉ ባለሀብቶችን እንዲስብ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
ከአንዳንድ የነዳጅ ድርጅቶች የሚቀርቡ የትርፍ ሕዳግ ጥያቄዎች እንዳሉ የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ‹‹ለዚህም እንደ አገር መፍትሄ መስጠት አለብን›› ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
ቢዝነሱ በባለሀብቶች ተመራጭ እንዲሆን የትርፍ ሕዳግ ማስተካከያ የሚሰራ ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡
በፊት በገበያ ላይ ልዩነት የነበራቸውን የኬሮሲን እና የናፍታ መሸጫ ዋጋ ችግር በማስከተሉ ከንግድ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ዋጋቸው እኩል እንዲሆን መደረጉን አስታውሰዋል፡፡
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ በአገር አቀፍ ደረጃ 700 ያህል ነዳጅ ማደያዎች ይገኛሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ ከተማ ከ250 በላይ ነዳጅ ማደያዎች ቢያስፈልጓትም፤ ያሉት ግን ከሚያስፈልገው ከግማሽ በታች 103 ብቻ ናቸው።
ምንጭ፡-አዲስ ዘመን