በኢትዮጵያ እየተቋቋሙ የሚገኙት አክሲዮን ማህበራት የባለሃብቱን እምነት እያጡ መምጣታቸውን በአክሲዮን ማህበራት ዘርፍ የተሠማሩ ባለድርሻ አካላት ገለጹ ።
የጃካራንዳ አክሲዮን ማህበር መስራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ደመላሽ ወጋየሁ እንደሚሉት ጃካራንዳ የግብርና ምርቶችን ለማቅረብ የተቋቋመ ድርጅት ሲሆን በኋላ በአመራርነት የተቀመጡ አካላት ከማህበሩ ጥቅም ይልቅ ለግል ጥቅም በማድላታቸው በመንኮታኮት ደረጃ ላይ መድረሱን ይናገራሉ ።
የህብር ስኳር አክሲዮን ማህበር ባለድርሻ የሆኑት አቶ መታሰቢያ ታፈረ በበኩላቸው ህብር ስኳር በአገሪቱ የስኳር እጥረት ችግርን በመገንዘብ የተቋቋመ ድርጅት መሆኑንና በኋላ በአመራር በኩል በሚፈጸሙ የአስተዳደራዊ ችግሮች ምክንያት ለማህበሩ መዳከም እንደ ምክንያት የሚጠቀስ መሆኑ ገልጸዋል ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የንግድ ህግ መምህሩ ረዳት ፕሮፌሰር ፈቃዱ ጴጥሮስ በሠጡት አስተያያት ባደጉት አገራት አክሲዮን ማህበራት ቁልፍ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሾች ሆነው እንደሚገኙ በመጠቆምበኢትዮጵያ ለማህበራቱ አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል የማይደረግላቸው ከሆነ የግለሰቦች መጠቀሚያ መሆናቸው የማይቀር ነው ብለዋል ።
እንደ ረዳት ፕሮፌሰር ፈቃዱ ገለጻ በአገሪቱ የሚቋቋሙ አክሲዮን ማህበራት ወደ ችግር ውስጥ እንዳይገቡ የወጡ የንግድ ህጎች በትክክል ስለመተግበራቸው የሚከታተል አካል ሊኖር ይገባል ፡፡
በንግድ ሚኒስቴር የአክስዮን፣ የንግድና ዘረፍ ማህበራት ክትትልና ድጋፍ ዳይሬክተር አቶ ኑረዲን ኢብራሂም በበኩላቸው አክሲዮን ማህበራቱን ለአባለሃብቱና ለአገር ዕድገት የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ ለማጠናከር የሚያስችል የመንግስት አደረጃጀት እየተዘረጋ በመሆኑ የድጋፍና ክትትል ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል ።
በኢትዮጵያ ከ1990ዎቹ ጀምሮ የሚቀቋሙት አክሲዮን ማህበራት ቁጥርና የካፒታል አቅም እያደገ መጥቷል ፡፡