አባይ ኢንዱስትሪ ልማት አክሲዮን ማህበር በ7 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ወጭ ለሚያስገነባው ሲሚንቶ ፋብሪካ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት በተገኙበት የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ።
በደጀን ከተማ አካባቢ ልዩ ስሙ ኮንቸር ሳሳበራይ እና ሜንጅየበዛ ቀበሌዎች የሚገነባው ፋብሪካ ሲጠናቀቅ፤ ለ1 ሺህ 690 ሰዎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ አድል ይፈጥራል ተብሏል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፥ ትናንት የመሰረት ድንጋዩን ባስቀመጡበት ወቅት እንደገለጹት ፋብሪካው የኢንዱስትሪ ልማት ሽግግርን ከማፋጠን ባሻገር መዋቅራዊ ለውጥ ለማማምጣት የሚያስችል ነው።
አክሲዮን ማህበሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ራሱን በማደራጀት ለሚገነባው ስሚንቶ ፋብሪካ 250 ሄክታር መሬት ከሶስተኛ ወገን ነጻ በማድረግ በኩል ከአካባቢው መስተዳድሮች ጋር መስራቱን ተናግረዋል።
ለፋብሪካው ጥሬ እቃ ማምረቻ የሚውል 3 ሺህ 600 ሄክታር ቦታ በአባይ ሸለቆ የተፈቀደለት ሲሆን፥ ከአካባቢው ልማት ጋር ተጣጥሞ እንዲሄድ አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግም አስረድተዋል።
የፋብሪካው ግንባታም በአራት ዓመት ከአራት ወራት ጊዜ ውስጥ ሲጠናቀቅ በቀን 5 ሺህ ቶን ሲሚንቶ እንደሚያመርት ይጠበቃል -(ኢዜአ) ።