በምስራቅ ሸዋ ዞን ህገወጥ ንግድን በህብረተሰብ ተሳትፎ ለመከላከል እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ

በተያዘው የበጀት ዓመት ህገ ወጥ የንግድን  በህብረተሰብ ተሳትፎ ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን የምስራቅ ሸዋ ዞን ንግድና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት ገለጿል።

ህገ ወጥ የንግድን ለመከላከል  ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ በቀበሌና በወረዳ ደረጃ ሲያካሄድ የቆየው ህዝባዊ የምክክር መድረክ ማጠቃለያ መርሃ ግብር  በአዳማ ከተማ ተካሂዷል።

በዚህ ወቅት የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ሽመልስ ሞላ እንዳሉት በህብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ ህገ ወጥ ንግድንና ኪራይ ሰብሳቢነትን በመግታት ስርዓት ለማሲያዝ ጥረት እየተደረገ ነው።

"በበጀት ዓመቱ ህገ ወጥ ንግድን ለመከላከልና ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ሳይኖር በተለያዩ ሸቀጦችና የምግብ እህሎች ላይ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት ይሰራል" ብለዋል።

ስራውን ለማሳካት ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የምክክር መድረክ መካሄዱን ተናግረዋል።

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በዞኑ ህገ ወጥ ንግድን ለመከላከል በተካሄደ ዘመቻ ከህግ አግባብ ውጭ ሲሰሩ የተገኙ 5 ሺህ 562 ነጋዴዎች መለየታቸውን አመልክተዋል።

"ከነጋዴዎቹ ውስጥ 4 ሺህ 442ቱ ህጋዊ የንግድ መረብ ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል" ያሉት ኃላፊው ወደ ህጋዊነት መምጣት ባልቻሉ ነጋዴዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደባቸው መሆኑን አስረድተዋል።

በጽህፈት ቤቱ የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ወገኔ ስዩም ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ በምስራቅ ሸዋ ለህገ ወጥ ንግድ መስፋፋት ምክንያት ያሏቸውን ጉዳዮች ጠቁመዋል።

የአስፈጻሚው አካል ቁርጠኝነት ማነስ፣ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና የህብረተሰቡ ተሳትፎ ደካማ መሆን ከጠቆሟቸው መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

"በዚህም ህብረተሰቡ በአቅርቦት እጥረት፣ በምርት ጥራት ጉድለትና በዋጋ መዋዥቅ እየተጎዳ ነው" ብለዋል ።

በተለይ ለዝቅተኛ የህብረተሰብ ክፍሎች በመንግስት ድጎማ የሚቀርቡ መሰረታዊ ሸቀጦች በቂ ያለመሆን ችግር ለመፍታት የሁሉም አካላት የነቃ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል ።

የኦሮሚያ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ተወካይ አቶ ፊጤ አበራ በበኩላቸው በክልሉ  ህገወጥ ንግድን ለመቆጣጠር  ሁሉም ወረዳዎችና ከተሞች በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ሳይኖር የዋጋ ንረት የሚፈጥሩትን ለመቆጣጠር የሸማቾ ማህበራትን ማጠናከርና ህብረተሰቡ በአደረጃጀቱ ህገ-ወጦችን እንዲከላከል ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።