በሚቀጥለው ዓመት 15 የሚሆኑ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ማምረት እንደሚገቡ ኮርፖሬሽኑ አስታወቀ

2012 ዓ.ም ማጠናቀቂያ 15 የኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ማምረት እንደሚገቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ።

በኮርፖሬሽኑ የኦፕሬሽንና ማኔጅመንት ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ሰለሞን  እንደተናገሩት፤ እስካሁን የሀዋሳ፣ የቦሌ ለሚ ቁጥር አንድ አይሲቲ፣ የመቐለ እና ኮምቦልቻ ፓርኮች ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ ሥራ ገብተዋል።

ከቀናት በፊት የተመረቀውን የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ ጨምሮ የጅማና የደብረ ብርሃን የኢንዱስትሪ ፓርኮች በሁለት ወራት ውስጥ ወደ ሥራ ይገባሉ ተብሏል፡፡

የቦሌ ለሚ ቁጥር ሁለት፣ የባህር ዳር፣ የድሬዳዋና የቂሊንጦ ፋርማስቲዩካል ፓርኮች በተያዘው በጀት ዓመት የሚጠናቀቁ መሆናቸውን ገልፀው  በተጨማሪም የአይሻ፣ የአረርቲ የአሶሳና ሠመራ ፓርኮች በዚሁ ዓመት ግንባታቸውን ለመጀመር የአዋጭነት ጥናቶቻቸው ተጠናቆ ወደ ስምምነት እየተገባ መሆኑን ተናግረዋል።

እስካሁን ባለው ተሞክሮ የአንድ ፓርክ ግንባታ ከዘጠኝ ወር እስከ አንድ ዓመት ይጠናቀቃል ያሉት ኃላፊው ሌሎቹም በዚሁ መሰረት በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ይጠናቀቃሉ ብለዋል፡፡

ፓርኮቹ የተለያዩ ምርቶችን የሚያመርቱ ቢሆንም በዋናነት መንግሥት በኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ ባስቀመጠው መሰረት በአልባሳትና ጨርቃ ጨርቅ፣ በህክምና መገልገያዎችና የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ላይ የሚያተኩሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል። (ምንጭ: አዲስ ዘመን)