የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአዲስ አበባ ከተማን እድገት ለማሳለጥ የበኩሉን ድርሻ መወጣት ይኖርበታል – ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአዲስ አበባ ከተማን እድገት በማገዝ  ሀገራዊ ድርሻን ማበርከት እንደሚገባው ምክትል ከንቲባ  ኢንጅነር ታከለ ኡማ ገለጹ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር  ምክትል ከንቲባ  ኢንጅነር ታከለ ኡማ እና  ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች  የኢትዮጵያ አየር መንገድን  አደረጃጀትና አሰራር ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡

ከጉብኝቱ በኋላ  ኢንጅነር ታከለ ኡማ እንደገለጹት  የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሁላችንም  ኩራት በመሆኑ  አብረን  በመስራት  ሁለንተናዊ  ለውጥ ማምጣት ይገባል፡፡

አየር መንገዱ   በጉብኝት  ምልከታው  አስገራሚ በመሆኑ  ሁሉም ኢትዮጵያዊ  ሊጎበኘው  የሚገባ ነው ካሉ በኋላ  በተቋሙ ላይ የሚደረገው ኢንቨስትመንት  የከተማውም ኢንቨስትመንት በመሆኑ በጋራ በመስራትና በማገዝ  ሀገራዊ ለውጡን  እናስቀጥላለን ሲሉ  ኢንጅነር ታከለ ኡማ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢ  አቶ አባዱላ ገመዳ በበኩላቸው አየር መንገዱ ከ50  አመታት በፊት የተቋቋመ መሆኑን ጠቁመው  በየጊዜው ደረጃውን ለማሳደግ እና  ለማስፋፋት  በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡

በመሆኑም ይህንን  አገራዊ ፕሮጀክት  ለሚቀጥለው ትውልድ ለማስተላለፍ  በመተጋገዝ በላቀ መንፈስ  መተግበር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር  መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ  አቶ ተወልደ ገብረ መድህን እንዲሁ ኢትዮጵያ የነጻነት  ተምሳሌትና የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ በመሆኗ ታላቅ ከተማ ነች ፤ ይህንንም ተከትሎ በአፍሪካ ህብረትም ሆነ በሌሎች ተገልጋዮች  የሚሰጠው አገልግሎት የላቀ እርካታ እያስገኘ ነው፡፡     

አሁን ያሉት የማስፋፊያ መሰረተ ልማቶች  ባለፉት 5 አመታት የተገነቡት ዘመናዊነትን የተላበሱ መሆናቸውን ጠቁመው በተለይ የውጭ ጎብኝዎችን  የቆይታ ጊዜ ለማራዘም  373 ክፍሎች ያሉት ባለ 5 ኮከብ  ሆቴል ተገንብቶ መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡/ዘገባው የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ነው/