የኮትሮባንድ እንቅስቃሴን ለመከላከል ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር ይገባል – ወይዘሮ አዳነች አቤቤ

የሀገሪቱን ፈጣን ልማት ለማደናቀፍና ሰላምን በማደፍረስ ከፍተኛ ተፅዕኖ እየተፈጠረ የሚገኘውን የኮትሮባንድ እንቅስቃሴ ለመከላከል ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር እንደሚገባ የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ አስታወቀዋል፡፡

የኮትሮባንድ እንቅስቃሴ እያሳደረ የሚገኘውን ሁለንተናዊ ተፅዕኖና በቀጣይ የመፍትሄ እርምጃዎች ዙሪያ የሚመክር ውይይት ትናንት በድሬዳዋ ተጀምሯል፡፡

የምስራቅ ተጎራባች ክልሎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የፌደራል ተቋማት በተሳተፉበት የውይይት መድረክ ላይ ሚኒስትሯ ወይዘሮ እንዳሉት በሀገሪቱ የታክስ ስወራ፣ የኮትሮባንድና ህገ-ወጥ ንግድ እንቅስቃሴዎች ህጋዊና ፍትሃዊ የንግድ ውድድር እንዳይጎለብት እንቅፋት ሆነዋል፡፡

ለልማት መዋል ይችል የነበረውን በቢሊዮን የሚገመት ገንዘብ እንዳይሰበሰብ ከማድረግ በተጨማሪ  የውጭና የሀገር ውስጥ ንግድና ኢንቨስትመንትን እየጎዳው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተለይ የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ አቅም ማዳከሙን ነው የገለፁት፡፡

ይህን በሀገር ዕድገትና ሰላም ላይ መርዝ እየረጨ የሚገኘውን ኮትሮባንድ በተቀናጀ መንገድ መከላከልና በቁጥጥር ሥር ማዋል እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን በበኩላቸው ኮትሮባንድን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል ሥርዓት የተዘረጋ ቢሆንም ችግሩን እንዲከላከሉ የተቋቋሙ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የተጣለባቸውን ኃላፊነት በሚፈለገው መጠን አልተወጡም፡፡