የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለሱዳንና ጅቡቲ ካቀረበው የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ከ28 ሚሊየን ዶላር ገቢ አገኘ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በአምስት ወራት ውስጥ ለሱዳንና ጅቡቲ ካቀረበው የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ 28 ሚሊየን 414 ሺህ 752 ዶላር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡

ከዚህ ውስጥ 17 ሚሊየን 500 ሺህ ዶላሩ ከጅቡቲ የተገኘ ሲሆን፥ ቀሪው ከሱዳን መሆኑን ገልጿል፡፡

ገቢው የተገኘው ከባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ጀምሮ እስከ ጥቅምት 2011 ባለው በአምስት ወራት ውስጥ መሆኑን ተቋሙ አስታውቋል፡፡

ኢትዮጵያ ታዳሽ የኤሌክትሪክ ኃይል በማልማት በምስራቅ አፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመፍጠር በስፋት እየሰራች መሆኑ ይታወቃል፡፡

በዚህም በቅርብ ጊዜያት ውስጥ ከሶማሌ ላንድ፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ እና ደቡብ ሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል ትስስር ለመፍጠር የሁለትዮሽ ግንኙነት በማድረግ ላይ ትገኛለች።

በቅርቡም ከኬንያ ጋር በኃይል ልማት ለመተሳሰር ባለ 500 ኪሎ ቮልት ከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡