የሥራ ፈጠራ ባለቤቶች የባንክ ብድር የሚያገኙበትን አሠራር ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ ነው

የሥራ ፈጠራ ባለቤቶች የፈጠራ ሓሳባቸውን ብቻ በማስያዝ የባንክ ብድር የሚያገኙበትን አሠራር ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ ነው ።

በዚህ ላይ የሚመክር መድረክ በኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሲሆን የስራ ፈጠራ ባለቤቶችና የፋይናንስ አካላት ተገኝተውበታል፡፡

ስራ ፈጣሪዎችን በማበረታታት የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያድግ ለማድረግ ያለመ የውይይት መድረክ እንደሆነም የጽ/ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኤርሚያስ የማነብርሀን ገልፀዋል።

የስራ ፈጠራ ባለቤቶች የፈጠራ ሀሳባቸውን ብቻ በማስያዝ የባንክ ብድር ማግኘት፣ የፋይናንስ አሰራር ምን ይመላል እና የሌሎች ሀገሮች ተሞክሮን በማጣቀስ  ጥናታዊ ፅሁፍ ቀርቧል፡፡

ጥናቱን ያቀረቡት የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ይልማ ካሳሁን እንደገለፁት በሀገራችን የፈጠራ ባለሙያዎች ንብረት ሳያስይዙ በፈጠራ ሀሳባቸው ብቻ ብድር የሚያገኙበት አሠራር ያለመኖሩ ፈጠራዎች እንዳያድጉ እንቅፋት ሲሆን ቆይቷል  ብለዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ የነበሩ የስራ ፈጠራ ባለቤቶች በሰጡት አስተያየት ሀገራችን በፈጠራ ስራ ወደፊት እንድትራመድ ለማስቻል ይህ አይነት የብድር አሰራር ተግባራዊ መሆን ይኖርበታል፤ ተግባራዊነቱም ባለድርሻ አካላት ማገዝ ይኖርባቸዋል ብለዋል ።

የፋይናንስ ባለሙያዎች በበኩላቸው  የፈጠራ ባለቤቶችን ከፋይናንስ ተቋማት በተጨማሪ መንግስት ፈንድ በመመደብ ሊደግፍ ይገባዋል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም  የፈጠራ ባለቤቶች ወደ ፋይናንስ ተቋማት ሲመጡ የፈጠራ ስራቸውን ብቻ ሳይሆን ያለውን አዋጭነትና ሌሎች የፋይናንስ ጥናቶችን አካተው ቢመጡ የሀሳባቸው ተቀባይነት ይጨምራል ሲሉ ገልፀዋል።

የፈጠራ ባለሙያዎችን ለማበረታታትና የኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚውን ለማሳደግ  የፋይናንስ ተቋማት የተለያዩ ሀገሮች ተሞክሮን ወደሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ በማምጣት ከፈጠራ ባለቤቶቹ ጋር በመሆን መስራት እንዳለባቸውና መንግስትም ሊያግዝ እንደሚገባው በውይይቱ ተገልጿል ።