የዘንድሮ የሞዴል ጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ኤግዚቢሽን የ4 ሚሊዮን ብር ሽያጭ ይኖረዋል ተባለ

የ2011 ዓም ሃገር አቀፍ የሞዴል ጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ኤግዚቢሽን እና ባዛር የ4 ሚሊዮን ብር ሽያጭ እንደሚኖረው ተገለጸ፡፡

ኤግዚቢሽን እና ባዛሩን አስመልክቶ የፌደራል የከተሞች የስራ እድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ በዛሬው እለት መግለጫ የሰጠ ሲሆን ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ 185 የጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች እና አስር አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች እንደሚሳተፉበትም ገልጿል፡፡

በማኑፋክቸሪንግ፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በእደ ጥበብ፣ በቴክኖሎጄ ፈጠራ እንዲሁም በምርት ዲዛይን ስራ የተሰማሩ አምራቾችና በጥቃቅን የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች የተመረቱ ምርቶችን ብቻ የሚያቀርቡ በኤግዚቢሽኑ የሚሳተፉ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡

በ2010 ዓም በ2ኛው ዙር በተካሄደው አገር አቀፍ ኤግዚቢሽን እና ባዛር ላልተሳተፉ ኢንተርፕራይዞች ቅድሚያ ይሰጣል፡፡

ከተሳታፊዎች መካከል 50 በመቶ ሴቶች ፤ 3 በመቶ የአካል ጉዳተኞች እንዲሁም 10 ተቋማት ሲሆኑ ምርትና አገልግሎታቸው ከ17፣ሺህ በላይ በሚሆን ተጠቃሚ ይጎበኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተጠቅሷል፡፡

ኤግዚቢሽኑ ኢንተርፕራይዞች ከተጠቃሚው ህብረተሰብ ጋር በሚያደርጉት ግንኙነት ዘላቂ የገበያ ትስስር ለመፍጠር የሚያሰችል ምቹ አጋጣሚ እንደሚፈጥርላቸው ይጠበቃል፡፡

ባህላዊ እና ዘመናዊ የጨርቃ ጨርቅ እና የቆዳ አልባሳት ምርት ውጤቶች፤ የእደ ጥበባትና ቅርጻቅርጽ ውጤቶች፤ የብረታብረት፣ የእንጨትና የኢንጅነሪንግ ስራዎችና ዉጤቶችእንዲሁም የአግሮ ፕሮሰሲንግ እና የከተማ ግብርና ውጤቶች በኤግዚቢሽን እና ባዛሩ ይቀርባሉ ተብሏል፡፡

ኤግዚቢሽን እና ባዛሩ ከታህሳስ 22 እስከ ታህሳስ 28 ድረስ ይቆያል፡፡