በህገ ወጥ መንገድ ለሽያጭ ሊቀርብ የነበረ 995 ሊትር ነዳጅ ተያዘ

በህገ ወጥ መንገድ ለሽያጭ ሊቀርብ የነበረ ግምቱ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ  995 ሊትር ቤኒዝን የኮንትሮባንድ ዕቃ ከህብረተሰብ በደረሰ ጥቆማ መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

እንደ ኮሚሽኑ ገለጻ፥ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ልዩ ቦታው በተለምዶ 7ኛ ሸንኮራ በረንዳ ተብሎ ከሚጠራ አካባቢ ከሚገኘው «ትዕግስት ብሩክ ቶታል ማደያ» ውስጥ ጥር 12 2011 ዓ.ም የተቋሙ ሰራተኞች ከህገ-ወጦች ጋር በመተባበር በ44 ጀሪካን 995 ሊትር ቤንዚን ከማደያው በመቅዳት ላይ እንዳሉ ከህዝብ በደረሰው ጥቆማ መሰረት የተቀዳውን ቤንዚን እና ሌላ ሊቀዳበት የነበረ 44 ባዶ ጀሪካን በቁጥጥር ስር ውሏል።

እንዲሁም አንድ አይሱዙ ተሽከርካሪን ከአምስት ተጠርጣሪዎች ጋር በቁጥጥር ስር ማዋሉን እና በምርመራ እያጣራ መሆኑን የክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ የወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ዲቪዚዮን ኃላፊ ኮማንደር ጌታነህ በቀለ ገልፃዋል።

በቁጥጥር ስር የዋለው ቤንዚን ከ11 ሺህ ብር በላይ ዋጋ እንደሚያወጣ ኮማንደር ጌታነህ በቀለ አስታውቀዋል።

በተያያዘ ዜና ጥር 13 ቀን 2011 ዓ.ም ምዕራብ ሆቴል አከባቢ ግምቱ ከ1 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ በኮንትሮባንድ እቃዎች ሲንቀሳቀስ የነበረ ተሽከርካሪን ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ በቁጥጥር ስር ኮማንደር ጌታነህ መግለፃቸውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።