ከ60 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ወጪ የተገነባው የስካይ ላይት ሆቴል ነገ ይመረቃል

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ60 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ወጪ ያስገነባው የስካይ ላይት ሆቴል በነገው ዕለት ተመርቆ ወደ ሥራ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

ስካይ ላይት ሆቴል ለሶስት አመታት ያህል የግንባታው ሥራ ሲከናወን የቆየ  ሲሆን ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት መሥጠት ሲጀምር  የባለ 5 ኮከብ ደረጃን ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል ።

ሆቴሉ በመላው ዓለም የሚገኙ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ትራንዚተሮችን ከማስተናገድ ረገድ ትልቁን ድርሻ እንደሚወጣ ተገልጿል፡፡

ሆቴሉ በአጠቃላይ 373 የማረፊያ ክፍሎች፣ አራት ደረጃቸውን የጠበቁ ሪስቶራንቶች፣ የመዋኛ ገንዳ፣ የአዳራሽ አገልግሎትና ሌሎችም ዘርፈ-ብዙ የሆቴል አገልግሎቶችን በሟሟላት ሀገሪቱ በትኩረት እየሠራች የሚትገኘውን የቱሪዝም ኢንዱስትሪን ይበልጥ  እንደሚያግዝምታምኖበታል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ እኤአ በ2025 በዓለምአቀፍ ደረጃ  እጅግ ተወዳዳሪ አየር መንገድ ለማድረግ የሚያደርገውን ጥረት ለማሳካት  መሰል የሆቴል ግንባታዎች ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን በአየር መንገዱ የመሠረተ ልማት ክፍል ኃላፊ አቶ አብርሃም ተስፋዬ ለዋልታ ተናግረዋል፡፡

በነገው ዕለት ተመርቆ ወደ ሥራ የሚገባው ስካይ ላይት ሆቴል የቱሪዝም ኮንፌረንሱን በማገዝም የጎላ አስተዋፅዖ አለው ተብሏል፡፡