ኢትዮጵያና ስፔን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነታቸውን የበለጠ ለማጠናከር ተስማሙ

ኢትዮጵያና ስፔን በመካከላቸው ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነትን የበለጠ በማጠናከር ለመስራት ተስማምተዋል።

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከስፔን አቻቸው ጆሴፍ ቦሬል ጋር የአገራቱን ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።

ኢትዮጵያ በፈጣን የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሽግግር ላይ እንደምትገኝ ከራሷ አልፎም በቀጠናው ሰላምና የኢኮኖሚ ውህደት እንዲሰፍን እየሰራች መሆኗን ዶክተር ወርቅነህ ለስፔኑ አቻቸው ገልጸዋል።

አገሪቱ በፖለቲካ ታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በውጭ አገራት የሚኖሩና ነፍጥ አንግበው መንግስትን ሲዋጉ የነበሩና በተቃውሞ የቆዩ የፖለቲካ ሃይሎች ወደ አገራቸው ተመልሰው ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንዲያካሂዱም ተደርጓል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከስፔን ጋር በንግድ፣ በኢንቨትመንትና በቱሪዝም ዘርፎች ተባብራ መስራት እንደምትፈልግም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ስፔን በግልና በአውሮፓ ህብረት በኩል በአፍሪካ በስደተኞች፣ በባህር ላይ ውንብድናና ሽብርተኝነትን በመዋጋት ረገድ ለምታደርገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው 30 በአፍሪካ የስፔን አምባሳደሮችን ለማነጋገር ማቀዳቸውም የሚደነቅ መሆኑን ዶክተር ወርቅነህ ገልጸዋል።

የስፔን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆሴፍ ቦሬል በበኩላቸው ስፔን ከአፍሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር እንደምፍትፈልግና የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውም የዚሁ አካል መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህ ስኬትም በአፍሪካ የተለያዩ አገራት ስፔንን ወክለው ከሚሰሩ 30 አምባሳደሮች ጋር በአዲስ አበባ ውይይት እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያና ስፔን የኢንቨስትመንት ትውውቅና የድርብ ቀረጥ የማስቀረት ስምምነት በማድረግ ግንኙነታቸውን የበለጠ ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸዋል።