ኢትዮጵያ የቡና ምርቷን በህንድ ሙምባይ አስተዋወቀች

ኢትዮጵያ በትላንትናው ዕለት በህንድ ሙምባይ በስታር ባክስ የምዕራብ ቀጠና አስተባባሪነት በተካሄደ ዝግጅት የቡና ምርቷን አስተዋውቃለች።

በሙምባይ የኢፌዴሪ ቆንሱል ጄኔራል አቶ ደመቀ አጥናፉ በዝግጅቱ ላይ “ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ወይም መናገሻ” በሚል ርዕስ ለተሳታፊዎች የመወያያ ጽሁፍ አቅርበዋል።

ቡና ከስያሜው ከፋ ከሚባል የኢትዮጵያ አካባቢ እንደተገኘና በዚህም ‘ኮፊ’ የሚል ስያሜ እንዳገኘ የገለጹት አቶ ደመቀ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከዓለም ቡና አምራችና ላኪ አገራት 5ኛ መሆኗን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በይርጋጨፌ፣ ሐረር፣ ሲዳማ፣ ጉጂ፣ ቴፒ፣ ጂማ እና ነቀምት አካባቢዎቿ በዓለም ደረጃ ተወዳጅና ተመራጭ ቡና እንደምታመርት ተናግረዋል።

በዝግጅቱ ላይ የኢትዮጵያ ባህላዊ የቡና አፈላል ስርዓት ለእይታ ቀርቧል፡፡ (ምንጭ፡-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ ጽ/ቤት)