የኢትዮጵያና የተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች የቢዝነስ ፎረም በአዲስ አበባ ተጀመረ

የኢትዮጵያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የቢዝነስ ፎረም ከ60 በላይ የዓረብ ኤምሬቶች የቢዝነስ ልዑክና የመንግስት ተወካዮች በተገኙበት በአዲስ አበባ ተጀምሯል።

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካኤል በፎረሙ መክፈቻ ንግግር አድርገዋል።

በንግግራቸውም ሀገራቱ ያዳበሩት የቆየ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የንግድና ኢንቨስትመንት ትብብራቸውን ለማሳደግ የመሰረት ድንጋይ ይሆናል ብለዋል።

ዶክተር አክሊሉ ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ምቹ መሆኗን ገልጸው ፎረሙ በሀገራቱ መካከል ያለውን ትስስር በማጠናከር ወደ ተግባራዊ የኢኮኖሚ ግንኙንት ለመለወጥ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የኢኮኖሚ ሚኒስቴር የውጭ ንግድ ምክትል ጸሃፊ አብዱላህ አል ሳሌህ በበኩላቸው፥ፎረሙ በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለመለየት እንደሚያስችል አንስተዋል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ ፎረሙ የሀገራቱን ግንኙነት በሁሉም ዘርፎች ለማጠናከር ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

አምባሳደር ምስጋኑ ኢትዮጵያ ያላት አቀማመጥ ወደ አካባቢው የገበያ መዳረሻዎች ምርቶችን ለመላክ አመቺ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይህም በሀገራቱ መካከል ቀጣይነት ያለው የንግድ ትስስር ለመፍጠር እንደሚያስችል ተገልጿል ፡፡

ምንጭ፡- የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር