ኢትዮጵያ በግል ሀብት ፈጠራ በዓለም ቀዳሚ ከሆኑ 3 አገራት አንዷ ሆነች – ጥናት

ኢትዮጵያ በግል ሀብት ፈጠራ ከዓለም 3ኛ መሆኗን አዲስ ጥናት አመለከተ፡፡
ኢትዮጵያ በመስኩ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቻይና እና ሞሪታኒያ ተቀድማ ሶስተኛ መሆኗን ‘ኒው ወርልድ ዌልዝ’ የተባለው የደቡብ አፍሪካ የጥናት ተቋም ይፋ ያደረገው ሪፖርት ጠቅሷል፡፡

የዜጎቿ ሀብት የመፍጠር አቅም እያደገ በመምጣቱ ኢትዮጵያ በመጪዎቹ ዓመታት በአፍሪካ ጠንካራ ተፎካካሪ የኢኮኖሚ ባለቤት ሆና እንደምትወጣ ጥናቱ ጠቅሷል፡፡

በዚህም በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ኢትዮጵያ የኬንያ ዋንኛ የኢኮኖሚ ተቀናቃኝ እንደምትሆን ተገምቷል፡፡

ጥናቱ እንደሚያሳየው በኬንያ የግል ሀብት ፈጠራ ችሎታ በየዓመቱ በ6 በመቶ ሲያድግ ቆይቶ እኤአ በ2018 የ64 በመቶ እድገት አስመዝግቧል፡፡

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ይኸው ምጣኔ በየዓመቱ በ10 በመቶ ሲያድግ ቆይቶ እኤአ በ2018 የ102 በመቶ እድገት ማስመዝገብ ችሏል፡፡ ሆኖም በኬንያ ያለው የግል ሀብት መጠን 104 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን በኢትዮጵያ ያለው ደግሞ 64 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ በግለሰቦች የተያዘው የሀብት መጠን 204 ትሪሊዮን ዶላር መድረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ 

(ምንጭ፦ ስታንዳርድ ሚዲያ)