ባለፉት ዘጠኝ ወራት 145.74 ቢሊዮን ብር ገቢ ተሰበሰበ

በተያዘው በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ የገቢዎች ሚኒስቴር፣ የጉምሩክ ኮሚሽን እና የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር 145 ነጥብ 74 ቢሊዮን ብር ገቢ ሰብስበዋል።
የገቢዎች ሚኒስቴርና የተጠሪ ተቋማት የ2011 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት አፈፃፀም በትላንትናው እለት በገመገሙበት ወቅት የገቢዎች ሚኒስትሯ ወይዘሮ አዳነች ሀቤቤ እንዳሉት አፈፃፀሙ 80 ነጥብ 87 በመቶ ሲሆን ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ12 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ወይም የ9 ነጥብ 07 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
ገቢው የተሰበሰበው ከውጭ ንግድ ቀረጥና ታክስ፣ ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች፣ ከሀገር ውስጥ ቀጥታ ታክስ እና ከሀገር ውስጥ ቀጥታ ካልሆነ ታክስ መሆኑን ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የገቢ ዕቅዱ ሙሉ በሙሉ እንዳይሳካ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች እንደነበሩ ተገልጿል፡፡
የሀገር ሰላም ባልተረጋጋበት፣ የወጪ ንግድ በተቀዛቀዘበት፣ የአሰራር ማሻሻያ እየተካሄደ በነበረበት ወቅት ይህን አፈፃፀም ሊመዘገብ የቻለው የአመራርና ሰራተኞች ቁርጠኝነት በመኖሩ እንደሆነ የገለፁ ሲሆን በቀሪ ወራት ርብርብ በማድረግ ወደ ገቢ ሊቀየሩ የሚችሉ አቅሞችን አሟጦ በመጠቀም የገቢ አሰባሰቡን ማሻሻል እንደሚገባ ሚኒስትሯ አስገንዝበዋል፡፡
በውይይቱ ወቅት ደረሰኝ የማይቆርጡ እና የሀሰተኛ ግብይት ደረሰኝ የሚያቀርቡና የንግድ ማጭበርበር የሚፈፅሙ ድርጅቶች ህግ የማስከበር ስራ መስራት፣ የውዝፍ ዕዳ አሰባሰብ የማሻሻል ስራዎች በቀጣይ ትኩረት እንደሚሰጣቸው በውይይቱ ላይ ተጠቅሷል፡፡

(ምንጭ፡- የገቢዎች ሚኒስቴር)