የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቱ የሸርዓ አማካሪዎችን ሰየመ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በፍጥነት እያደገ ላለዉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቱ የሸርዓ አማካሪዎችን ሰየመ፡፡

ባንኩ ለዋልታ በላከዉ መግለጫ ዶ/ር ጀይላን ከድር የአማካሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ሼክ ሙሓመድ ሐመዲን ማክትል ሰብሳቢ አድርጎ መሰየሙን ገልጿል፡፡

እንዲሁም ተባባሪ ፕሮፌሰር ኑር አብዲ፣ ዶክተር መሓመድ ዜይን፣ ኡስታዝ አወል አበዱልወሃብ በአባልነት ሰይሟል፡፡

አዲስ የተሰየሙት የአማካሪ ኮሚቴ አባላትም ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትን ለሕብረተሰቡ ተደራሽና ተአማኒ ለማድረግ ከባንኩ ጎን በመቆም የበኩላቸዉን ድርሻ እንደሚወጡ ገልፀዋል፡፡

ሚያዚያ 30 ቀን 2011 ዓ.ም በባንኩ ዋን መስሪያ ቤት በተካሄደ ስነ-ስርዓት በህብረተሰቡ ዉስት ተቀባይነት ያላቸዉ አምስት ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት አማካሪ ኮሚቴ አባላት ከባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ ከአቶ ባጫ ጊና የስራ መመሪያ ተቀብለዋል፡፡

በስነ-ስርዓቱ ላይ የባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ እንደተናገሩት በወለድ ምክንያት ከባንክ አገልግሎት ርቀዉ የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ለማድረግና ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት የበኩሉን እገዛ እንዲያደርግ አዲስ ተሰየሙት የሸርዓ ኮሚቴ አባላት ትኩረት ሰጥተዉ እንዲሰሩ ጠይቀዋል፡፡

የሸርዓ አምከሪ ኮሚቴዉ ሰብሳቢ የሆኑት ዶክተር ጄይላን ከድር በበኩላቸዉ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎትን በስፋት ተደራሽ ለማድረግ የያዘዉን ዕቅድ ለማሳካት እዉቀት እና ልምዳቸዉን ተጠቅመዉ እንደሚሰሩ ነዉ የተናገሩት፡፡

በዕለቱም የአማካሪ ኮሚቴዉ አባላት ከባንኩ የስራ አመራር አባላትና ከባንኩ የወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት የስራ መሪዎች ጋር ትዉዉቅ  አድርገዋል፡፡