ኢትዮጵያ ከዓመታዊ የቡና ምርቷ ውስጥ 50% የሚሆነውን ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ታውላለች

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ከተውጣጡ የልኡካን ቡድን አባላት ጋር በአፍሪካ የቡና ፍጆታ ማሳደግ በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ዛሬ በአዲስ አበባ ባደረጉት ምክክር ኢትዮጵያ በአመት ከምታመርተው ቡና ውስጥ 50 በመቶ የሚሆነው ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውል መሆኑ ተገለፀ፡፡

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ በውይይት መድረኩ ላይ እንደገለጹት፣ የአፍሪካ ሀገራት ገበሬዎችና አምራቾች ከቡና ምርት ተጠቃሚ ባለመሆናቸው፣ ከኢትዮጵያ ልምድ መቅሰም ይችላሉ፡፡

አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገራት የሚያመርቱትን ቡና በጥሬው ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ እንጂ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የማይጠቀሙ በመሆናቸው የዓለም የቡና ገበያ በሚወርድበት ጊዜ ተጠቃሚነታቸው እንደሚቀንስ ይነገራል፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ አብዛኛዎቹ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ቡናን በብዛት የሚያመርቱ ቢሆኑም፣ እሴት ጨምሮ አለመሸጥና የሀገር ውስጥ ተጠቃሚዎቻቸው አናሳ በመሆኑ ተጠቃሚ መሆን አልቻሉም፡፡

በአሜሪካና በአውሮፓ ካለው ገበያ በተጨማሪ አብዛኛዎች የአፍሪካ ሀገራት እርስ በእርስቸው የገበያ ትስስር በመፍጠር አምራቹን ተጠቃሚ ማድረግ የሚቻልበትም ዕድል መፍጠር እንደሚገባ የልዑካን ቡድኑ አባላት ገልጸዋል፡፡