ኢትዮ ቴሌኮም በ2011 በጀት ዓመት 36.3 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ

ኢትዮ ቴሌኮም የ2011 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸሙን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ የሰጡት የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ ፍሬህይወት ታምሩ በ2011 በጀት ዓመት 36 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል።

የተገኘው ገቢ የእቅዱን 80 በመቶ ያሳካ መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ ፍሬህይወት፥ ገቢው ከአምናው ጋር ሲነጻጸር 7 በመቶ ብልጫ አሳይቷል ነው ያሉት።

የደንበኞችን የመግዛት አቅም በማገናዘብና የቴሌኮም አገልግሎት አጠቃቀምን ለማሻሻል እንዲሁም የደንበኞችን እርካታ ለመጨመር ከ40 እስከ 50 በመቶ የሚደርስ ከፍተኛ የታሪፍ ቅናሽ በሁሉም ምርትና አገልግሎቶች ላይ መደረጉንም አንስተዋል።

በዚህ የታሪፍ ቅናሽም 19 በመቶ የድምፅ ትራፊክና 130 በመቶ የዳታ ትራፊክ ዕድገት መመዝገቡን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ኢትዮ-ቴሌኮም ባለፉት ሶስት ዓመታት ሳይከፍል የቆየውን ውዝፍ የ9 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር እዳ መክፈሉን አስታውቀዋል።

ዘገባው የኢዜአ ነው፡፡