ከሐምሌ 1/2011 ጀምሮ ከ197 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ኮትሮባንድ መያዙን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ

ኮሚሽኑ በሀገር አቀፍ የጸረ-ኮትሮባንድ ዘመቻው ከሐምሌ 1/2011 ጀምሮ ከ197 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ኮትሮባንድ መያዙን አስታወቀ።
የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ በኢትዮጵያ በተጠናቀቀዉ በጀት ዓመት የተሻለ የፀረ ኮትሮባንድ ዘመቻ የተካሄደበት ዓመት እንደነበር አስታውሰዋል።

በዓመቱ የተስተዋለውን የተጠናከረ ጸረ ኮንትሮ ባንድ ዘመቻ በተሻለ መልኩ ለማስፈፀምም በም/ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ግብረ ኃይል ከሐምሌ 1/2011 ዓ.ም ጀምሮ ስራ መጀመሩን በማስታወስ፤ የኮትሮባንዲስቶችን እንቅስቃሴዎች ለመግታት ኮሚሽኑ ከክልሎች፣ ከፀጥታ አካላትና ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

ኮሚሽኑ በሐገራዊዉ የጸረ ኮትሮባንድ ዘመቻ ከሐምሌ 1 ጀምሮ ከ197 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ኮትሮባንድ መያዙን አስታውቀዋል።

በኮሚሽኑ መግለጫ መሰረት በሐምሌ ወር ብቻ ከ134.3 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ኮትሮባንድ የተያዘ ሲሆን፤ የነሃሴ ወር ከገባ ጀምሮም 63 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ኮትሮባድ መያዙን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

በትላንትናዉ ምሽትም አህመድ ሀሰን አህሚድ የተባለ ግለሰብ ወርቅና የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦችን ከሀገር ለማስወጣት ሲሞክር በሶማሌ ክልል ሞምባስ ኬላ ላይ በቁጥጥር ስር ዉሏል ተብሏል፡፡
መንግስት የጀመረዉ የፀረ ኮትሮባንድ ዘመቻ ከፍተኛ በመሆኑም ኮትሮባንዲስቶቹ በአፀፋዉ የኃይል እርምጃ በመዉሰዳቸዉ የሰዎች ህይወት ማለፉንም ተናግረዋል፡፡

በተለያዩ ግዜያት የሚያዙ የኮትሮባንድ እቃዎችና ገንዘቦች በህጋዊ መንገድ ለመንግስት ገቢ እንደሚደረጉ ለጋዜጠኞች የገለጹት ኮሚሽነር ደበሌ፤ በተጠናቀቀዉ የ2011 በጀት ዓመት ባጠቃላይ ከ1.6 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመት የኮንትሮ ባንድ ዕቃዎችን መያዙን አስታውቀዋል።

መንግስት በህገወጥ ጦር መሳሪያ ዝዉዉርና በሌሎች የኮትሮባንድ እንቅስቃሴዎች ላይ የጀመረዉን ዘመቻ በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥል በመግለጽ፤ በቀጣይ በሚኖረው ዘመቻ ህብረተሰቡ የላቀ ትብብር እና ድጋፍ እንዲያደርግ ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡