በ400 ሚሊዮን ብር የተገዙት የኦዳ አውቶቡሶች ከወር በኋላ አገልግሎት ይጀምራሉ

ኦዳ የተቀናጀ የትራንስፖርት አገልግሎት በ400 ሚሊዮን ብር ከአውሮፓ ገበያ የገዛቸውን 50 አውቶቡሶች ከአንድ ወር በኋላ ሙሉ በሙሉ ወደ አገልግሎት እንደሚገቡ ተጠቆመ፡፡

ተቋሙ በየብስ ትራንስፖርት አገልግሎት ምስራቅ አፍሪካን ለማስተሳሰር እየሰራ እንደሚገኝ የኦዳ የተቀናጀ የትራንስፖርት አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ እሸቱ ዘለቀ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ገልፀዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት 50 አውቶቡሶች ከአውሮፓ ገበያ በመግዛት የህብረተሰቡን የትራንስፖርት ችግር ለማቃለል እየሰራ ይገኛል፡፡ ከ50ዎቹ አውቶቡሶች ውስጥ አስቀድሞ አራቱን አገር ቤት በማስገባት ሙከራ እየተደረገ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

የተቀሩት 46 አውቶቡሶች አዳማ መድረሳቸውንናከአንድ ወር በኋላ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ አገልግሎት እንደሚሰጡ ገልፀዋል፡፡

እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ፤ አውቶቡሶቹ የስዊድን ኩባንያ ከሆነው ቮልቮ የተገዙ ሲሆን፤ እያንዳንዳቸው ስምንት ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎባቸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት አራቱ አውቶቡሶች በድሬዳዋ፣ በነቀምት፣ በሻሸመኔና በሀዋሳ መስመሮች አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው፡፡

የኦዳ አውቶቡሶች ትራንስፖርት ሙሉ በሙሉ አገልግሎት ሲጀምርም በአገሪቱ በአራቱም አቅጣጫዎች የስምሪት አገልግሎት ይሰጣል፡፡

አውቶቡሶቹ ዘመናዊ የመቆጣጠሪያ መሳሪያ የሚገጠምላቸው ሲሆን ቁጥጥሩን በአንድ ማዕከል ሆኖ ለመምራት የሚያስችል ሲስተም እየተዘረጋ ነው፡፡

ተቋሙ እየጀመረ ባለው የትራንስፖርት አገልግሎትም እስካሁን ሹፌሮችንና ኦፊሰሮችን ጨምሮ 200 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ እድል ፈጥሯል፡፡