ኬንያ  ድፍድፍ ነዳጅ ወደ ተለያዩ ሀገራት መላክ ጀመረች

ኬንያ  ድፍድፍ ነዳጅ ወደ ተለያዩ ሀገራት መላክ መጀመሯን የሀገሪቱን መገናኛ ብዙሃንን ጠቅሶ አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

ኬንያ በታሪኳ የመጀመሪያ የተባለውን ድፍድፍ ነዳጅ የጫነች መርከቧን የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታን ጨምሮ የተለያዩ ባለስልጣናት በተገኙበት ከሞምባሳ ወደብ መነሳቷ ተገልጿል፡፡

ኬንያ የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦ የሌላት ሀገር በመሆኗ ድፍድፍ ነዳጁ በሰሜን ምስራቅ ኬንያ ቱርካና ከሚገኘው የነዳጅ ማውጫ ቦታ 850 ኪሎ ሜትር በተሽከርካሪ ተጉዞ ሞምባሳ እንደደረሰም ነው የተነገረው፡፡

ሀገሪቱ የነዳጅ ማስተላለፊያ ቱቦውን ለመዘርጋት ከዩጋንዳ ጋር ይዛው የነበረው እቅድ፤ ዩጋንዳ ከታንዛኒያ ጋር ውል በመጀመሯ ምክንያት ሳይሳካ መቅረቱም ነው የተነገረው፡፡
 

አሁን ኬንያ ጅበዘርፉ የጀመረችው እንቅስቃሴም በቀጠናው ያለውን የነዳጅ ልማት ዘርፍን ለማሳደግ ትልቅ መነቃቃትን የሚፈጥር ነው ተብሏል ፡፡

በቀጣይም ሀገሪቱ የተጣራ የነዳጅ ምርቶችን ከአምስት አመታት በኋላ ወደ ውጪ ሀገራት የመላክ ውጥን እንደያዘችም ዘገባው አትቷል፡፡

ኬንያ በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ ከነዳጅ ከ84 ሚሊየን ዶላር በላይ ገቢ ታገኛለች ተብሎም ይጠበቃል፡፡

እንደ ቱሎው ካምፓኒ ግምት ከሆነ በኬንያ ቱርካና የነዳጅ ማውጫ ቦታ 560 ሚሊየን በርሜል የነዳጅ ክምችት የሚገኝ ሲሆን፤ ከአውሮፓዊያኑ 2022 ጀምሮ በየቀኑ 100 ሺህ በርሜል ነዳጅ ያመርታል ተብሎም ይገመታል።

ተቀማጭነቱን በሀገር እንግሊዝ ያደረገው የቻይና ኩባንያ 'ኬምቻይና ዩ ኬ ሊሚትድ' የመጀመሪያውን 240 ሺህ በርሜል የነዳጅ ድፍድፍ ለመግዛት ጨረታውን ማሸነፉም ተነግሯል፡፡