በህግ ተገዢ ያለመሆን ችግሮች በገቢ አሰባሰቡ ላይ ትልቅ ፈተና መደቀናቸውን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታወቀ

 በህግ ተገዢነት ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮች በገቢ አሰባሰቡ ላይ ትልቅ ፈተና መሆኑን የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ተናገሩ፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴር ከምእራብ አዲስ አበባ ግብር ከፋዮች ጋር በተወያየበት ወቅት ነው ሚኒስትሯ ይህን ያሉት፡፡

በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል ከክብር ሁሉ የላቀ ክብር መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሯ ፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በ2012 ታላላቅ እቅዶችን አቅዶ ወደ ስራ በመግባት ለግብር ከፋዩ ማህበረሰብ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት በሙሉ ተነሳሽነት ስራ መጀመሩን  ጠቁመዋል፡፡

ታማኝና ለህግ ተገዥ የሆኑ ግብር ከፋዮች ምስጋና ይገባቸዋል ያሉት ሚኒስትሯ፤ አሁንም ወደ ንግድ መረብ ስርዓቱ ያልገቡና ታክስን በማጭበርበር እና ጭራሽ ባለ መክፈል የሚንቀሳቀሱ አካላት መኖራቸዉን አንስተዋል፡፡

በታክስ ስወራ ላይ የተሰማሩ አካላትን ለህግ ተገዥ እንዲሆኑ በማደረጉ ጉዳይ ላይ ከዚህ በኋላ ድርድር እንደማይኖርም አስረድተዋል፡፡

የሚኒስቴሩ የምዕራብ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት በ2011 በጀት ዓመት 9.47 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 8 ነጥብ 61 ቢሊየን ብር በመሰብሰብ የእቅዱን 91 በመቶ ማሳካቱን በዚሁ ወቅት ተገልጿል፡፡

በ2012 በጀት ዓመትም 10 ነጥብ 76 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ እየሰራ መሆኑን የቅርንጫፍ ፅ/ቤቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ያሬድ ፍቃደ ተናግረዋል፡፡

መስሪያ ቤቱ ያሉበትን ተግዳሮቶች ለመፍታት መዘጋጀቱ የተገለጸ ሲሆን ፤ ግብር ከፋዮችም የድርሻቸውን እንዲወጡ ነው የተጠየቀው፡፡