ህጋዊ የንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው አትክልት ያለደረሰኝ ሲሸጡ የተገኙ 30 የጭነት ተሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን ፖሊስ አስታወቀ

የከተማው ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ የሚመራው ግብረ ሃይል በአራዳ ክፍለ ከተማ ፒያሳ አትክልት ተራ ህገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን ለመከላከል ባደረገው ድንገተኛ ቁጥጥር 30 አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬ የጫኑ 30 አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪዎች ከነጭነታቸው በግብረ- ሀይሉ የተያዙት ህጋዊ ንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸውና ያለደረሰኝ ሲሸጡ በመገኘታቸው ነው፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን እንዳስታወቀው የከተማው ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ የሚመራውና የአራዳ ከፍለ ከተማ አስተዳደር፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የተለያዩ ቢሮዎች ፤ ደንብ ማስከበርና ፖሊስ ኮሚሽኑ የተካተቱበት ግብረ ሃይል ጳጉሜ 5 ለ 6 አጥቢያ ከሌሊቱ 9 ሰዓት እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ባደረገው ቁጥጥር ከህጋዊ የንግድ ስርዓት ውጪ ሰው ሰራሽ የዋጋ ንረት እንዲከሰት ለማድረግ በሞከሩ አካላት ላይ እርምጃ ወስዷል ፡፡

በ30ዎቹ አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪዎች ላይ ተጭነው የተያዙት የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎች ህጋዊ ስርአቱን ጠብቆ በጨረታ እንደሚሸጡም ታውቋል፡፡

ህገወጥነትን የመከላከልና ህጋዊነትን የማስፈን ሃላፊነት ያለበት ፖሊስ ኮሚሽኑ በቀጣይም ከባለድርሻ አካላት ጋር የቅንጅት ስራውን አጠናክሮ ህጋዊ እርምጃ መውሰዱን እንደሚቀጥልና ህብረተሰቡ በዚህ ዙሪያ አስፈላጊውን መረጃ በመስጠት መተባበር እንዳለበት አሳስቧል፡፡