ሚኒስቴሩ  ከከፍተኛ ግብር ከፋዮች ጋር ምክክር እያካሄደ ነዉ

በገቢዎች ሚኒስቴር የከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ  ፅ/ቤት ከከፍተኛ ግብር ከፋዮች ጋር ምክክር እያደረገ ነዉ፡፡

የምክክር መድረኩን በንግግር የከፈቱት የገቢዎች ሚኒስቴር የህግ ተገዢነት ዘርፍ ሚኒስትር ድኤታ አቶ ዘመዴ ተፈራ በ2011 በጀት አመት የግብር ከፋዩና የተለያዩ አካላትን ሃሳብ መነሻ በማድረግ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሪፎርም ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸዉን አንስተዋል፡፡

ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አንፃር የታክስ ህግ አስተዳድርን የማዘመን፤ የአደረጃጀትና አሰራር ለዉጥ በማድረግ በግብር ከፋዩም ዘንድ ግብርን በታማኝነትና በአግባቡ የሚከፍሉትን እዉቅና የመስጠትና የመሸለም መርሃ ግብሮች መከናወናቸውንም አስታውሰዋል፡፡

በተጨማሪም ስለ ግብር ህጉ እና አሰራር የግንዛቤ እጥረት ያለባቸዉን የማስተማርና የግንዛቤ መፍጠሪያ ኩነቶችን በማዘጋጀት ግንዛቤዉ እንዲኖራቸዉ የማድረግ ስራ እና ህጉንና አሰራሩን እያወቁ ሆን ብለዉ ግብርና ታክስን የማጭበርበር ድርጊት በሚፈጽሙት ላይ ህግ የማስከበር ስራ ተከናዉኖ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል፡፡

ይህ አሰራርም በዘንድሮዉ በጀት አመትም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አንስተዋል፡፡

የከፍተኛ ግብር ከፋዮች  ቅርንጫፍ  ፅ/ቤት የ2011 በጀት አመት አፈፃፀም የቀረበ ሲሆን፤  በአጠቃላይ በሚኒስቴር መስሪ ቤቱ በተደረጉ ሪፎርሞችና የተቀረፉ ችግሮች እንዲሁም አሁን እያጋጠሙ ባሉ ተግዳሮቶች ላይ ዉይይት እየተደረገእንደሚገኝ ከገቢዎች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡