የነዳጅ ሥራዎች ፖሊሲና አዋጅ ተዘጋጀ

በኢትዮጵያ የነዳጅ ፍለጋን ለማጠናከር፣ በአገሪቱ ያለውን የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ለማወቅና ወደ ምርት ለመግባት የሚያስችል የነዳጅ ሥራዎች ፖሊሲና አዋጅ ተዘጋጀ።

በማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር በተዘጋጁት የነዳጅ ፖሊሲና አዋጅ ረቂቆች ላይ የመከረ የባለድርሻ አካላት ውይይት በትናንትናው እለት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በተለይ የፖሊሲው መውጣት በኢትዮጵያ የሚካሄደውን የነዳጅ ፍለጋ ስራ ከማጠናከር ባለፈ የአገሪቱን የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ለማወቅና ወደ ምርት ለማስገባት የላቀ ጠቀሜታ አለው ሲሉ በሚኒስቴሩ የነዳጅ ፈቃድና አስተዳደር ዳይሬክተር ዶክተር ቀጸላ ታደሰ በውይይቱ ላይ አስረድተዋል።

የነዳጅ አልሚዎች ተሳትፎን ውጤታማ ማድረግ፣ በዘርፉ ልማት ዙሪያ በፌዴራልና ክልል መንግስታት መካከል የተቀናጀ አሰራር መዘርጋት ከፖሊሲው ዓለማዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

ከዘርፉ ጋር በተያያዘ የአገር ውስጥና የቀጣናውን የገበያ ዕድል በመዳሰስ የተሻለ የገበያ አማራጭ መፈለግና ተወዳዳሪ የሆነ የገበያ ስርዓት መዘርጋትም እንዲሁ ሌሎቹ ዓላማዎች ናቸው።

ፖሊሲው ኢትዮጵያዊያን በዘርፉ ስልጠና የሚወስዱበትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ማረጋገጥ የሚቻልበት አቅጣጫዎችን ያመላከተ ነው ብለዋል።

በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ለረጅም ጊዜ የቆየ ከመሆኑ ጋር የአገሪቷን ወቅታዊ ሁኔታ የሚያስተናግድ ባለመሆኑ እንዲሻሻል ሆኗል ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት የተረቀቀው የነዳጅ ሥራዎች አዋጅ በ1978 ዓ.ም የወጣውን አዋጅ የሚተካ እንደሆነ  ዶክተር ቀፀላ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ ዶክተር ኳንግ ቱትላም በበኩላቸው አገሪቷ በዘርፉ ፖሊሲ አልነበረታም ሲሉ ጠቅሰው፤ በዚህም የተነሳ በነዳጅ ፍለጋ ላይ የሚሰማሩ ኩባንያዎችን በሚጠበቀው መጠን መሳብ አለመቻሉን ተናግረዋል።

ዶክተር ኳንግ እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በነዳጅ ፍለጋ ተግባር ተሰማርተው የሚገኙት ኩባንያዎች ከአምስት አይበልጡም።

በመሆኑም በመስኩ ፖሊሲና የነዳጅ ሥራዎች ረቂቅ መዘጋጀቱ እነዚህን የመሳሰሉ መሰረታዊ ችግሮችን እንደሚፈታ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በሶማሌ ክልል ነዳጅ መገኘቱን የሚኒስቴሩ መረጃ የሚያመላክት ሲሆን፥ በክልሉ በኦጋዴን አካባቢ 6 ነጥብ 3 ትሪሊየን ኪዩቢክ ጫማ ድፍድፍ ነዳጅ ክምችት አለ ተብሏል።