የባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ በዚህ ወር መጨረሻ ሥራ ይጀምራል

የባህርዳር ኢንዱስትሪ ፓርክ የመጀመሪያው የግንባታ ምእራፍ ተጠናቆ በመስከረም ወር መጨረሻ ሥራ እንደሚጀምር የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገለፀ።

የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አማረ አስገዶም በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ የፓርኩ የመጀመሪያው ምእራፍ ግንባታ በ75 ሄክታር መሬት ላይ በውሉ መሰረት በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል።

በዚሁ ምእራፍ የተገነቡት የፋብሪካ ሼዶችም ስምንት ሲሆኑ፤ በመጀመሪያው ዙር ለ4 ሺህ በሁለተኛው ዙር ደግሞ ለ8ት ሺህ ዜጎች የሥራ እድል ይፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

እንደ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ፤ በመጀመሪያው ምእራፍ የፓርኩ ግንባታ የሚያስፈልገው የኃይል መጠን ስምንት ሜጋ ዋት በመሆኑ በኃይል አቅርቦቱ ዙሪያ ጥናት ተሰርቶ ተጠናቋል።

የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሰጪ አካሉም የኤሌክትሪክ ምሰሶ ተከላዎችን ጀምሯል።

በዚህ ወር መጨረሻም ለፓርኩ የሚያስፈልገው የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን ይቀርባል ተብሎ ይታሰባል።