የእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፉን ለማጠናከር ያለመ የንግድ ትርኢት በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው

የእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፉን ለማጠናከር ያለመ የንግድ ትርኢት በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

የንግድ ትርኢቱ የእንስሳት መኖ ልማት አምራቾችን፣ መኖ አቀናባሪዎችና ሸማቾችን ለማስተሳሰር ያለመ ነው ተብሏል፡፡

በአማራ ክልል የሚገኙ 22 ወተት፣ የስጋና የእንቁላል እንስሳት መኖ አምራች እንዲሁም መኖ አቀናባሪ ማኅበራት ምርቶቻቸውን ለዕይታ አቅርበዋል።

የንግድ ትርኢቱን የአማራ ክልል እንስሳት ሀብት ልማት ኤጀንሲ ከኤሲዲ አይ ቮካ ጋር በመተባበር ነው ያዘጋጀው።

የአማራ ክልል እንስሳት ሀብት ልማት ኤጀንሲ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ፈንቴ ቢሻው በክልሉ በርካታ የእንስሳት ሀብት ቢኖርም የሚጠበቀውን ያክል ምርት እየሰጠ አለመሆኑን አስረድተዋል።

ዘርፉን ለማሳደግም የሌሎች አጋር አካላት ቅንጅታዊ አሠራር ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
በእንስሳት ልማት ዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን በመቅረፍ ውጤታማ ለመሆን ዓላማ ያደረገ የግማሽ ቀን የፓናል ውይይት ይካሄዳል ተብሎም ይጠበቃል። መረጃው የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት ነው፡፡