ሆራይዘን ኤክስፕረስ ባልደራሱ የተባለ የጥቅል እቃ መልእክት አገልግሎት ይፋ አደረገ

ሆራይዘን ኤክስፕረስ ሰርቪስ ኃ/ተ/ማ የኢኮሜርስ አገልግሎት ዘረፍን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ባልደራሱ የተባለ የጥቅል እቃ መልእክት አገልግሎት ይፋ አደረገ፡፡

አገልግሎቱ ቀልጣፋ፣ ጊዜ እና ወጪ ቆጣቢ ከመሆኑም ባሻገር ለ10 ሺ ወጣቶች የስራ እድልን ይፈጥራል ተብሏል፡፡

ድርጅቱ ይፋ ባደረገው የጥቅል እቃ መልእክት አገልግሎት ላይ በከተማዋ የሚገኙ ከ10 ሺ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ እድል የሚፈጥር ሲሆን ከተለያዩ ድርጅቶች ጋርም አብሮ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

የሆራይዘን ኤክስፕረስ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ዮናስ አምደጺዮን እንደገለጹት ከዶክመንት ጀምሮ ማንኛውንም አይነት ቀላል እና ከባድ እቃዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ፣ በፍጥነት እና በታማኝነት በማድረስ በሃገሪቷ ኢኮኖሚ ላይ አዎንታዊ ተፅእኖ ይኖረዋል፡፡

ባልደራሱ ተንቀሳቃሽ ንብረት ላላቸው ደንበኞች ንብረቶቻቸውንም ሆነ ገቢዎቻቸውን በቀጥታ የሚቆጣጠሩበት ስርአት እንዲያካትት ሆኖ መሰራቱ ተገልጿል፡፡

በዚህም ማንኛውም ተሸከርካሪ ያላቸው ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች በተወሰነ መልኩ የሚጠቀሙባቸውን ንብረቶቻቸውን ከባልደራሱ ጋር በጋራ በመስራት ተጨማሪ ገቢ ማግኘት እንደሚያስችላቸው ነው ዋና ስራ አስፈፃሚው የተናገሩት፡፡

አጋር ድርጅቶች አገልግሎቱ በወጪ ቅነሳ፣ ደህንነት እና ቀልጣፋ አገልግሎት ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን የበኩላቸውን እንደሚያደርጉ ገልፀዋል፡፡