የኢትዮጵያ እና ሱዳን የቢዝነስ ፎረም እየተካሄደ ነው

የሱዳን ቢዝነስ ካውንስል ያዘጋጀው ከሱዳን እና ኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት ዘርፍ የተወጣጡ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች እና የግል ባለሀብቶች የሚሳተፉበት የንግድና የኢንቨስትመንት ፎረም ዛሬ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ በፎረሙ መክፈቻ ሥነስርዓቱ ላይ እንደተናገሩት ፎረሙ የሁለቱን ሀገራት የንግድ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር ያስችላል።   

የሁለቱ አገራት ታሪካዊ፣ መልከዓምድራዊ፣ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሐብታዊ ግንኙነታቸው ጠንካራ መሆኑን ገልጸው፣ በቀጣይ በቱሪዝም፣ በግብርና ማቀነባበሪያ እና በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ኢትዮጵያ ማመቻቸቷን ሚኒስትሩ ተናገረዋል፡፡   

የኢትዮጵያና ሱዳን ጥምር ኮሚቴ ተቋቁሞ በቋሚነት ይሰራል ብለዋል፡፡ በግሉ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ የሱዳን ባለሐብቶች እንዲሳተፉም አቶ አሕመድ ጥሪ አቅርበዋል፡፡  

የሱዳን የቢዝነስ ፎረም ፕሬዚዳንት ዋግዲ ሚርጋኒ በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ መንግስትና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሱዳን ሰላም እንዲሰፍን ላበረከቱት አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል። የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች በማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ዙሪያ ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው መሆኑንም አክለዋል።

በምግብ ዘይት ምርትና የወተት ተዋፅኦዎችን በማቀነባባር መስኮች ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው በፎረሙ ላይ የተሳተፉት የሱዳን ባለሀብቶች ተናግረዋል፡፡  

በቢዝነስ ፎረሙ የሁለቱ ሀገራት የንግድ ሚኒስትሮች፣ አምባሳደሮች፣ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ ባለሐብቶች እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።