ወደ ግል ከሚዞሩት የስኳር ፋብሪካዎች የ13ቱ የቴክኒክ ምርመራና የስድስቱ የዋጋ ትመና በመጠናቀቅ ላይ ነው

በመንግስት ይዞታ ስር ያሉ ኢንተርፕራይዞችን ወደ ግል ይዞታ የማዘዋወር ሂደት ግልፅነት በሰፈነበትና የሀገር ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መልኩ እየተተገበረ እንደሚገኝ የገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የስኳር ፋብሪካዎችን ወደ ግል ይዞታ በማዞር ምርታማ በማድረግ ወደ ውጪ ለመላክ በሚያሥችል ቁመና ላይ እንዲገኙ ለማስቻል እርምጃዎች እየተወሰዱ እንደሚገኝም ተገልጿል ፡፡

የስኳር ፋብሪካዎችን የፕራይቬታይዜሽን ሂደት ለማመቻቸት የ13ቱ የቴክኒክ ምርመራ እንዲሁም የስድስቱ የዋጋ ትመና በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ሚኒስቴሩ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡

የሀገሪቱን ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት የቴሌኮም ዘርፍ ማሻሻያን እየተገበረ ሲሆን ፤ከዚህ ውስጥ የኢትዮ ቴሌኮም አሰራር ዘመናዊ እንዲሆንና ሰፊ ተደራሽነት እንዲኖረው የተለያዩ ተግባራት እየተተገበሩ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ሆኖም በአለምአቀፍ መመዘኛዎች ኢንተርፕራይዙ የሚጠበቀው ተወዳዳሪነት ላይ ባለመድረሱ መንግስት ከፍተኛ ባለድርሻነቱን ይዞ በመቀጠል በከፊል ወደ ግል ይዞታ የማዞር ሂደትም ተጀምሯል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮ ቴሌኮምን ወደ ግል የማዞር ሂደት ገለልተኛ የግብይት ሂደት አማካሪ ለመቅጠር እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡

ዘርፉን ለውድድር ክፍት ለማድረግና ነፃና ገለልተኛ በሆነ ሁኔታ የከፊል ፕራይቬታይዜሽን ሂደቱን ለማስፈፀም የኮሙኒኬሽን ተቆጣጣሪ ባለስልጣን እንዲቋቋም ሆኗል፡፡

አሁን ላይ ተቆጣጣሪ ባለስልጣኑ ሁለት ተጨማሪ የቴሌኮሙኒኬሽን ኦፕሬተር ድርጅቶችን በግልፅ ጨረታ በማወዳደር ወደ ገበያ እንዲገቡ እያደረገ ሲሆን፤ በ2012 ሶስተኛ ሩብ ዓመት ሂደቱ እንደሚጠናቀቅም ነው ሚኒስቴሩ የገለፀው፡፡