ኢትዮጵያና ማሌዢያ የንግድና ኢንቨስትመንት ልውውጥን ለማጎልበት ተስማሙ

ኢትዮጵያና ማሌዢያ በዓመት ከ160 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር በላይ የሚገመተውን የንግድ ኢንቨስትመንት ልውውጥ ለማጎልበት ከስምምነት ደርሰዋል፡፡  

በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ልውውጥ ለማጠናከር የማሌዢያ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር የተመራ ልዑክ በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት እያደረገ ይገኛል፡፡

የልዑክ ቡድኑ ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡

ከውይይቱ በኋላ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት ሚኒስትር ዴኤታው ወደ ማሌዢያ ያደላውን የሁለቱ ሀገራት የንግድ ልውውጥ ለማስተካከል በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር መካሄዱን ገልጸዋል፡፡

በኢንቨስትመንት እና አቅም ግንባታ ላይ በጋራ ለመስራትም በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት መካሄዱንና ከስምምነት መደረሱን አምባሳደር ምስጋኑ ተናግረዋል፡፡

የማሌዢያ ልዑክ ከተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች ጋርም ተጨማሪ ውይይት እንደሚያካሂድ ታውቋል፡፡   

ኢትዮጵያ በዓመት ከ159 ሚሊየን ዶላር በላይ የሚገመቱ ምርቶችን ከማሌዢያ ትገዛለች ነው የተባለው፡፡