የማሌዢያ የንግድ ልኡካን ቡድን ከኢትዮጵያ አቻው ጋር ተወያየ

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከማሌዢያ የንግድ ልኡካን ቡድን ጋር በንግድ ግንኙነትና ማስፋፊያ ዙሪያ ውይይት አካሂዷል፡፡

በውይይቱ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የንግድ ማስፋፊያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ እና የማሌዢያ ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡

በእለቱም የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ የውይይቱን ዓላማ ሲገልጹ ‘’በሁለቱ ሃገራት መካከከል ያለውን የንግድ ልውውጥ ለማስፋትና ለማጠናከር ነው’’ ብለዋል፡፡

የማሌዢያ ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ሚስ ተሬሳ ኮክ በበኩላቸው በሁለቱ ሃገራት መካከል ያለውን የቆየ የንግድ ግንኙነት ሚዛኑን የጠበቀ እንዲሆን አጥብቀው እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

በተለይ ከማሌዢያ ወደ ኢትዮጲያ የሚገቡ የተለያዩ ምርቶች አለማቀፍዊ የጥራት ደረጃቸውን እንዲጠብቁ ክትትል የሚደረግባቸው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ሁለቱ ሃገራት ከንግዱ ባሻገር በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ በጋራ ለመስራት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን መግለፃቸውን ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡