የካናዳ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ

የኢፌዴሪ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ የካናዳ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ አዋጭ የኢንቨስትመንት እድሎች ላይ በስፋት እንዲሳተፉ ትናንት በካናዳ ሞንትሪያል ከተማ ኤምባሰው ከኩቤክ መንግስት የኢኮኖሚ እና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር ጋር በትብብር ባዘጋጁት የኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ጥሪ አቅርበዋል።

አምባሳደሯ በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ለተከታታይ ዓመታት ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ የባለሃብቶችንና ታዋቂ ዓለም አቀፍ ተቋማትን ትኩረት መሳብ የቻለች አገር መሆኗን ገልጸዋል።

የእድገቱን ዘላቂነት ለማረጋገጥና ሰፊ የስራ እድሎችን ለመፍጠር መንግስት የውጭ ባለሃብቶችን ለመሳብ ዘርፈ ብዙ የማሻሻያ ፕሮግራሞችን ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝም አምበሳደሯ አብራርተዋል።

በተለይም የ”Ease of Doing Business” ለማሻሻል እና የውጭ ኢንቨስተሮችን የሚያጋጥሙ መዋቅራዊና ከኢንቨስትመንት ህገ-ደንብ ጋር ተያይዘው ያሉ ማነቆዎችን ለመፍታት በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ከዚህ ቀደም ለውጭ ባለሃብቶች ዝግ የነበሩ ሴክተሮች ጭምር ክፍት እየተደረጉ መሆናቸውን በመጥቀስ፣ የካናዳ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ውስጥ መዋዕለነዋያቸውን በማፍሰስ አገሪቷን በመጥቀም ለራሳቸውም ተጠቃሚ የሚሆኑበት ወሳኝ ምዕራፍ መፈጠሩን አምባሳደር ናሲሴ አውስተዋል።

በኢንቨስትመንት ፎረሙ ላይ ከ30 በላይ በማዕድን፣ ኢነርጂ፣ ICT፣ መሠረተ ልማት ግንባታ፣ ቱሪዝም እና በማማከር አገልግሎት ላይ የተሠማሩ ባለሃብቶች የተገኙ ሲሆን፣ የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት እድሎች የሚያሳይ ገለጻ እና የማዕድን ሃብት እና የቱሪዝም መስህቦች የሚያሳዩ ቪዲዮዎች ቀርበዋል። ገለጸውን ተከትሎ ጥያቄ እና መልስ እንዲሁም የአንድ ለአንድ ውይይት ተካሂዷል።

ባለሃብቶቹም በቀረበው ገለጸ በአገራችን የኢንቨስትመንት እድሎች ለመሣተፍ ፍላጎት ያሳዩ ሲሆን፣ ተጨማሪ ጥናት ለማካሄድ የባለሃብቶች ቡድን በቀጣይ በየካቲት ወር 2012 ዓም በአገራችን የቅድመ-ኢንቨስትመንት ጉብኝት እንደሚያደርግ መገለፁን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።